ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በቻይና ሪፐብሊከ የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዴኤታ ሱን ማኦሊ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በቻይና ሪፐብሊከ የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዴኤታ ሱን ማኦሊ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በቻይና ሪፐብሊክ የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዴኤታ ሱን ማኦሊ ከተመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ኮሚሽነር ጄነራሉ በከፍተኛ አመራር ደረጃ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና በቻይና ሪፐብሊክ የህዝብ ደህንነት ሚኒስቴር መካከል የተካሄደው ውይይት የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑን መግለፃቸውን ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
የሁለትዮሽ ትብብሩ በአመራሩ ቁርጠኝነት እየተጠናከረ መምጣቱንና የሁለቱን የፖሊስ ተቋማት ግንኙነት ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት እያሳደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡
በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው የሕግ ማስከበር ትብብር ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ በመቀጠሉ የእርስ በርስ የመረጃ ልውውጥ፣ የአቅም ግንባታ እና በተለያዩ የድጋፍ መስኮች እየተደረገ ያለው ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን መናገራቸውም በመረጃው ተመላክቷል።
በተጨማሪም ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች በውይይታቸው በኢትዮጵያ Belt and Road ፕሮጀክቶች ደኅንነት (the security of the Belt and Road Projects in Ethiopia) ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውም ተገልጿል።
በቻይና ሪፐብሊክ የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዴኤታ ሱን ማኦሊ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነው ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በተለያዩ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን መናገራቸውም ተመላክቷል።
አያይዘውም ኢትዮ-ቻይና በሕግ ማስከበር የትብብር ማዕከል (Ethio-China law enforcement cooperation center) በኢትዮጵያ በመክፈት ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ያላቸውን ቁርጠኝነት መግለፃቸውም ተጠቁሟል፡፡
በቻይና ሪፐብሊክ የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ዴኤታ የተመራው ልዑክ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት ማካሄዱም ተገልጿል፡፡
በግንባታ ሂደት ላይ ያሉትን የፎረንሲክ ሳይንስ ኢንስቲትዩት እና ባለ 5 ኮኮብ የኢንተርናሽናል ፖሊስ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሂደት ተዘዋውረው መመልከታቸውም ተመላክቷል፡፡
በዚህ ወቅትም በተለያዩ ማቴሪያል እና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ለመደገፍ ቃል መግባታቸውም እንዲሁ፡፡