ቀጥታ፡

79 አባላት ያሉት የሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ የቢዝነስ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ሊጎበኝ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 27/2016(ኢዜአ)፦ በሳውዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የተመራ 79 አባላትን የያዘ የሳዑዲ አረቢያ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ሊጎበኝ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ገለጹ።

ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ዓላማ ያደረገ መሆኑን አምባሳደር ነብዩ ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ ዛሬ ማታ አዲስ አበባ እንደሚገባና በሚኖረው የሶስት ቀናት ቆይታም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የማምረቻ ቦታዎች ይጎበኛል ብለዋል።

 

በሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች በኢትዮጵያ ስላሉት ምቹ የኢንቨስትመንትና ንግድ አማራጮች ለባለሀብቶቹ ገለፃ የሚደረግበት የኢትዮ-ሳውዲ አረቢያ የቢዝነስ የምክክር መድረክ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

የልዑካን ቡድኑ በግብርና፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም፣ በሀይል ማምረት፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በሌሎች ቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ያሉትን እድሎች ለመገንዘብ እንደሚፈልግም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በሳውዲ አረቢያ አቻው መካከል የመግባቢያ ስምምነት ይፈረማል ተብሎ እንደሚጠበቅም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም