ቀጥታ፡

በሰሜን ጎጃምና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት የተሰማራው ኮር በጽንፈኛው ቡድን ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦በሰሜን ጎጃምና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት የተሰማራው ኮር ጽንፈኛውን ቡድን ከህዝብ ነጥሎ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

ኮሩ በተሰማራባቸው በሰሜን ጎጃምና አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ጽንፈኛው ላይ የተቀናጀ ስምሪት በማድረግ ውጤታማ የኦፕሬሽን ስራ መከናወኑ ተገልጿል፡፡

የኮሩ ዘመቻ ሃላፊ ሻለቃ አረጋኸኝ አለሙ ጽንፈኛው ቡድን ሀይሉን ከተለያዩ ቦታዎች አሰባስቦ በሊበን በላሊበላ በዴንሳ ባታ በደለከስ በጥሩ ብርሃን በሸራታ አካባቢዎች ተደራጅቶ እንቅስቃሴ ቢጀምርም ሰራዊቱ ባደረገው የተቀናጀ ዘመቻ ከባድ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶበታል ብለዋል።

በመሆኑም ቅጣው የተባለ የጽንፈኛው ከፍተኛ አመራርን ጨምሮ 42 የጽንፈኛው ታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን ዘጠኝ መማረካቸውን ተገልጿል።


 

እንዲሁም ሁለት ፒ ኬ ኤም መትረየስ አንድ ተተካይ 40 ጎራሽ ዘጠኝ ኤ ኬ ኤም ክላሽ ሰባት ኋላ ቀር መሳሪያ አንድ የግንኙነት ሬዲዮ 02 ተሽከርካሪ አንድ ሞተር ሳይክል በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

በደለከስ እና በጥሩ ብርሃን የጽንፈኛው ቡድን ማሰልጠኛና የሎጀስቲክስ ማከማቻ ማዕከሉ የተመታ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡

በላሊበላ ጽንፈኛው ቡድን ገንዘብ ካልከፈላችሁ አልለቅም በማለት በገጠር ቀበሌ ውስጥ ታግተው የነበሩ 14 ንፁሃን ዜጎች በአሰሳና ፍተሻ ስምሪት ከታገቱበት ቦታ ማስለቀቅ እንደተቻለ ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


 

ሰራዊቱ ከክልሉ ጥምር ሀይል ጋር በመቀናጀት የጥፋት ቡድኑን ከህዝብ ነጥሎ እርምጃ የመውሰድ ተልዕኮውን ለመፈጸም ማንኛውንም አይነት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መሰናክሎችን በጽናትና በጀግንነት እየተሻገር የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ በሙሉ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ የኮሩ ዘመቻ ሀላፊ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም