ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎቻቸውን ለይተው አጠናቀቁ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ባለድርሻ አካላት ዛሬ ከሰዓት በተካሄደው መርሐ-ግብር አጀንዳዎቻቸውን ለይተው ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ እያካሄደ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ የምክክር ምዕራፍ ለስድስተኛ ቀን ዛሬም ቀጥሎ ውሏል፡፡

አምስቱ የምክክር ባለድርሻ አካላት ትላንት እና ዛሬ ከሰዓት በፊት በነበረው መርሃ-ግብር የአጀንዳ ሀሳቦቻቸውን በቡድን ሆነው ሲያጠናቅሩና ሲያደራጁ ቆይተዋል፡፡


 

ባለድርሻ አካላቱ ያጠናቀሯቸውን እና ያደራጇቸውን አጀንዳዎች በቃለ-ጉባኤ በማዘጋጀት ለአጠቃላይ መድረኩ የሚያቀርቡላቸውን ተወካይ ግለሰቦችንም መርጠዋል፡፡

ዛሬ ከሰአት በተካሄደው መርሃ-ግብር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቡድን ሆነው ተስማምተው ያደራጇቸውን አጀንዳዎች በመረጧቸው ተወካዮች አማካኝነት ለጋራ መድረኩ አቅርበዋል፡፡


 

ከዚህ በኋላ በሚኖረው መርሃ-ግብር የባለድርሻ አካላቱ ወኪሎች ከሞደሬተሮች ጋር በመሆን የሁሉንም አጀንዳዎች በጋራ ሆነው አስቸኳይነትን፣ አስፈላጊነትን እና ወካይነትን ከግምት በማስገባት በየፈርጁ እንደሚያደራጁ ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በነገው ዕለትም በየፈርጁ የተደራጁት አጀንዳዎች የአዲስ አበባ ከተማ አጀንዳ ሆነው ለምልዓተ ጉባኤው ከቀረቡ በኋላ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተገኙበት የምክክር መድረክ እንደሚካሔድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም