የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የሚያከናውናቸውን ተግባራት ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የሚያከናውናቸውን ተግባራት ያጠናክራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የጀመራቸውን የጥናትና የምርምር ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዘጠነኛውን ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ማካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በተለያዩ ምሁራን የተከናወኑ የምርምር ሥራዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።
የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አለማየሁ ደበበ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በጉባኤ በተለያዩ ዘርፎች የተሰሩ ከ40 በላይ ጥናታዊ ምርምሮች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።
በመርኃ ግብሩ በልዩ ልዩ ርእሰ ጉዳዮች የሚሰሩ ጥናቶች ምን ያህል ችግር ፈቺ ናቸው የሚለውን በመገምገም ለመንግሥት ፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ውጤቶች እንደሚለዩ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከተሰጡት አበይት ተልእኮዎች መካከል በመንግሥት ተቋማት አወቃቀርና አሰራር፣ በሰራተኞችና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች በሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ምርምር ማካሄድ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ዓመታዊው የምርምር ጉባኤ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በምርምር የሚለዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጥናት በሚቀመጡ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር የመንግሥት አሰራር እንዲዘመን ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ብሎም ብቁ የሰው ኃይል እንዲኖር የጀመራቸውን የጥናትና የምርምር ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዩኒቨርሲቲው የሚያወጣቸው የምርምር ሥራዎች ወደ ተግባር እንዲለወጡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።