ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬትን ለማስቀጠል የሚያስችሉ የአቬዬሽን ደኅንነት የማስጠበቅ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል

 አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦ የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓት ለማዘመንና የክትትል ማዕቀፎችን ለማጠናከር የሚሰሩ ሥራዎች የአየር መንገዱ ስኬት ትልቅ አብርክቶ እያደረጉ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ገለጸ።

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስተባባሪነት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታስተናግደው ሀገራዊ የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዓለም አቀፍ ኦዲት በአዲስ አበባ መደረግ ጀምሯል። 

ዓለም አቀፍ ኦዲቱ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያና በሌሎች የአገር ውስጥ አየር ማረፊያዎች ከዛሬ ግንቦት 26 እስከ ሰኔ 6 ቀን 2016 ዓ.ም እንደሚደረግ ተገልጿል። 

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ሲሳይ ቶላ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ኩራት እንዲሆን ካስቻሉ ምክንያቶች መካከል ደኅንነቱ ተጠበቀ የአቬዬሽን አገልግሎት በመስጠቱ ነው ብለዋል።  

የኢትዮጵያ መንግሥትም የአየር መንገዱን የአቬዬሽን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ ዘመኑን በሚመጥን ቴክኖሎጂ  እንዲሁም በሰው ኃይል መታጠቁን አስረድተዋል።

በፈጣን ዕድገትና ተለዋዋጭ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የአቬዬሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚመጥን ጠንካራ አመራርና የሰው ኃይል በማደራጀት የክትትልና ድጋፍ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ዘርፍ ዳይሬክተር አስራት ቀጀላ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ብቁ የሰው ኃይል በማሰማራት ደኅንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በእነዚሀ ተቋማት የተደረጉ  ኦዲቶች ኢትዮጵያ በዘርፉ ተጠያቂነትን ለማስፈን ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም ለዘርፉ ደንብና መመሪያ ያላትን ተገዥነት ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።   

በመርኃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ሲቪል አቬይሽን ድርጅት ልዑካንና ባለሙያዎች እንዲሁም የአቪዬሽን ደኅንነት ኦዲተሮች ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም