ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት የቀጣናውን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው - ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማት ያለውን ቀጣናዊ ፋይዳ በመገንዘብ የተጠናከረ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የአፍሪካን የታዳሽ ሀይል አቅርቦት ለማሳደግ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የሚመክር "ለአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ትብብርን ማቀላጠፍ" Accelerated Partinership for Renewables in Africa/ APRA ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በዓለም አቀፉ የታዳሽ ሀይል ኤጀንሲ አማካኝነት በኮፕ 28 ጉባኤ ወቅት እንዲተገበር የተወሰነለት "ለአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ትብብርን ማቀላጠፍ" መርኃ ግብር ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡

በአሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ጀርመንና ዴንማርክ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው  መርኃ ግብር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሰባት የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡


 

"ለአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ትብብርን ማቀላጠፍ" መርኃ ግብር የገንዘብ፣ የቴክኒክና የግሉን ዘርፈ ተሳትፎ በማሳደግ ለዘርፉ ልማት እገዛ የሚያደርግ ነው፡፡

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መርኃ ግብሩ አፍሪካ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንድታውል የሚያግዝ ነው፡፡

የዓለም አቀፉን የታዳሽ ኃይል ኤጀንሲ መረጃ ዋቢ በማድረግ አፍሪካ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በታዳሽ ኃይል ልማት በዓለም ኢንቨስትመንት ያላት ተሳትፎ ከሁለት በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከታዳሽ ሀይል እስከ 60 ጊጋ ዋት ሀይል ማመንጨት የሚችል ጸጋ እንዳላት ገልጸው፤ ጥቅም ላይ የዋለው ግን ከ10 በመቶ በታች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያን እምቅ የታዳሽ ሀይል አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል ተቋም መገንባት እና የፋይናንስ አቅርቦት ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የታዳሽ ኃይል ዘርፉን መጠቀም የሚያስችሉ ህጎችና አሰራሮች ከጠንካራ ተቋም ጋር ገቢራዊ መደረጋቸውን ገልጸው፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሀይድሮ ፓወር፣ ነፋስና ጸሀይ ሀይል ልማት ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለጎረቤት ሀገራት 13 ሺህ ጊጋ ዋት ሀይል ማቅረቧን ጠቅሰው፤ የታዳሽ ኃይል ልማትን መደገፍ የቀጠናውን ሀገራት መደገፍ ነው ብለዋል፡፡


 

በዓለም አቀፉ የታዳሽ ሀይል ኤጀንሲ የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ትብብር ማቀላጠፍ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳፊያቱ አልዙማ፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት ድጋፍ ከሚደረግላቸው ሰባት የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሀይድሮ ፓወር እና እንፋሎትን ጨምሮ በታዳሽ ኃይል ሀብት እምቅ አቅም ያላት በመሆኗ ለቀጠናው ሀገራት ተስፋ ናት ብለዋል፡፡

የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ትብብርን ማቀላጠፍ መርኃ ግብር የተመረጡ ሀገራትን በፋይናንስ፤በቴክኒክና የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ኪራ ስሚዝ፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት በቀጠናው ተጠቃሽ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የታዳሽ ኃይል ልማት በአንድ ሀገር ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ዴንማርክ ለፕሮጀክቱም ሆነ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን ኃላፊ ፈርዲናንድ ቮን ዌይ፤ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልን ጥቅም ላይ ለማዋል የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት መጠቀም መጀመሯ ለዘርፉ ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

በመሆኑም የተጀመረውን የታዳሽ ኃይል ልማት ከግብ ለማድረስ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጎን ትቆማለች ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም