ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተደራሽነትና ፍትሃዊ የዜጎች ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተደራሽነትና ፍትሃዊ የዜጎችን ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ባንኩ የ2016 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸሙንና የአምስት አመት የሪፎርም ትግበራን በተመለከተ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት፤ ባለፉት አምስት የሪፎርም ትግበራ ዓመታት የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች ውጤታማ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ባንኩ ከነበረበት 39 ነጥብ 6 በመቶ የተበላሸ ብድርን በማስተካከል ወደ 3 ነጥብ 7 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በወሰደው ማሻሻያም አጠቃላይ ካፒታሉ 39 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን አሴቱ ደግሞ 179 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡

በበጀት አመቱ ዘጠኝ ወራት ከአራት ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን ገልጸው፤ ባንኩ ከነበረበት ኪሳራ ወጥቶ እዚህ ውጤት ላይ መድረሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።

ልማት ባንኩ ትኩረት የተሰጣቸውን የልማት ዘርፎች በመለየት ለደንበኞቹ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ብድር እና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባንኩ የዜጎችን ተደራሽነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ 12 የነበሩትን ዲስትሪክቶች ወደ 24፣ ቅርጫፍ መስሪያ ቤቶችን ከ76 ወደ 101 ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም የስራ ሃሳብ ፋይናንስ ወይም(አይዲያ ፋይናንስ)፣ ከወለድ ነጻ አገልግሎት፣ ለሴት አምራቾች የተለየ የብድር አገልግሎት፣ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት በመስጠት ተደራሽነትና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሃመድ አብዱ በበኩላቸው በአምስት አመት የሪፎርም ትግበራ የተገኙ መልካም ልምዶችን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸውን አሰራሮች ለማሻሻል በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተለይም የተበላሸ የዕዳ ጫናን በማቃለል ትርፍ ማስመዝገብ የተቻለበትን ውጤታማ ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

ወጣቶችን በሊዚ ፋይናንስ 20/80 አሰራር መሰረት የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ፣ ብድር የማስመለስ ስራን ጨምሮ የዜጎችን የፋይናንስ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የተደራሽነትና ፍትሃዊነትን የማስፋት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ባንኩ የዲጂታላይዜሽን ስራ ከመተግበር አንጻር የሚታዩበትን ክፍተቶች በፍጥነት በማሻሻል አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም