ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን በፈጠራና ቴክኖሎጂ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር ለማድረግ ለስታርትአፖች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን በፈጠራና ቴክኖሎጂ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር ለማድረግ ለስታርትአፖች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

የግሎባል ስታርትአፕ አዋርድስ አካል የሆነው ኢትዮጵያ ስታርትአፕ አዋርድስ መክፈቻ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የለውጡ መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምእራፍ የሚያሸጋግሩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበጋ መስኖ ስንዴ፤ በአረንጓዴ ልማትና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን በዚህ ረገድ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ የሀገር ልማት ሁለንተናዊ ሞተር ለሆኑ ስታርትአፖች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡


 

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ የላቁ ሀገራት በሁሉም መስክ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያም ይህንን በመገንዘብ ለስታርትአፕ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለስታርትአፕ ሁለንተናዊ እድገት የፖሊሲ እርምጃዎችንና በተቋማት ቅንጅት የሚተገበሩ ኢኒሼቲቮችን ይፋ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

ለአብነትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋ በሆነውና ለአንድ ወር በቆየው ብሔራዊ የስታርትአፕ ሁነት ከ300 በላይ ስታርትአፖች የተሳተፉ ሲሆን፣ ልምድ ልውውጥና ውድድር እንደተደረገበት አንስተዋል።

በወቅቱም ለስታርትአፖች ምቹ ምህዳር የሚፈጥሩ የተለያዩ የፖሊሲ ውሳኔዎች ይፋ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የወጣቶችን እምቅ አቅም በመጠቀም በዓለሞ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ስታርትአፖችን ለመፍጠር በቅንጅት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ሰጪነት ጥቅምት 2016 ከግሎባል ኢኖቬሽን ኢኒሼቲቭ ጋር በመተባበር የአፍሪካ ስታትርትአፕ ሽልማትን ማዘጋጀቷን አንስተው፥ ይህም ለሀገር በቀልና ለአፍሪካ ስታርትአፖች መበረታታት ዕድል እንደፈጠረ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የመላው አፍሪካ ስታርትአፕ ውድድርንና ሽልማትን ጥቅምት 2017 እንድታዘጋጅ መመረጧን ጠቅሰው፥ በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ ልጆች ልቀው እንደሚወጡ ይጠበቃል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ወጣቶች በጎ ሀሳብና ጉልበት ለሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል።


 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው በኢትዮጵያ ለኢኖቬሽንና ፈጠራ ስራዎች የተሰጠው ትኩረት ስታርትአፖች እንዲስፋፉ ምቹ እድል እየፈጠረ መሆኑን ገለጸዋል፡፡

በዚህም የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ስራዎችና ስታርትአፖች ወደ ገበያው እየተቀላቀሉ መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም