የተፋጠነ አጋርነት ለተዳሽ ኢነርጂ ልማት በአፍሪካ በሚል መሪቃል ምክክር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የተፋጠነ አጋርነት ለተዳሽ ኢነርጂ ልማት በአፍሪካ በሚል መሪቃል ምክክር ተካሄደ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 26/2016 (ኢዜአ)፦ የተፋጠነ አጋርነት ለታዳሽ ኢነርጂ ልማት በአፍሪካ በሚል መሪቃል የምክክር መድረክ ተካሄደ።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የታዳሽ ኢነርጂ ፍላጎትን በተግባር ለማሳደግ በሴፕቴምበር 2023 በናይሮቢ ኬንያ የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ መጀመሩን አስታውሰዋል።
ምክክሩ ከአለምአቀፍ የታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በሀገራችን መዘጋጀቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ ኃይል፣ የንፋስ ሀይልና የጸሀይ ሀይል አቅም ኢነርጂን ለማሸጋገርና ለማሳለጥ ጠቃሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
የታዳሽ ኢነርጂ ሀብቶችን መጠቀም የአፍሪካ የኢነርጂ እጥረትን ከመቀነሱ ባሻገር ለአየር ንብረት የማይበገር ኢንዱስትሪ እና የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን ያስችላል ብለዋል።
አፍሪካ ያላትን ከፍተኛ የታዳሽ ኢነርጂ ሀብት ክምችት ለመጠቀም የሚያስችል የተመቻቸ የኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ አቅርቦት ውስንነቶች የ2063 አጀንዳ ለማስፈጸም ተግዳሮት መሆኑንም አንስተዋል።
የኢነርጂ አጋርነት ለማጠናከር ድጋፍ ያደረጉት የዴንማርክ፣ የጀርመን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትሰ፣ የአሜሪካ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ሚኒስትሩ አመስግነዋል።
ምክክሩ ሁሉን አቀፍ የጋራ የማስፈፀም ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሀግብር ለመወሰን የሚያስችል በመሆኑ ተሳታፊዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
