የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበርና ኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበርና ኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሥምምነት ተፈራረሙ።
ሥምምነቱን የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) እና ኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) ፈርመውታል።
ሥምምነቱ ሁለቱ ተቋማት አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ያስችላቸዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሥምምነቱ በጋራ በመሥራት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ያስችላል።
ጭነት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ጨምሮ ሌሎች የደንበኞችን ጥያቄ በዘላቂነት ለመፍታትና ለተጠቃሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችልም ነው ያብራሩት።
ሥምምነቱ በጋራ ያሉ አቅሞችን በማሰባሰብም ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዲ ዘነበ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሥምምነቱን ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የሎጂስቲክ ዘርፉን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።