ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ጊኒ ቢሳው አቀና

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ቢሳው ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ወደ መዲናዋ ቢሳው ዛሬ ረፋድ ላይ አምርቷል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ብሔራዊ ቡድኑ ከጊኒ ቢሳውና ጅቡቲ ለሚያደርጋቸው የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ከግንቦት 19 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

አሰልጣኝ ገብረመድህን ጥሪ ካደረጉላቸው ተጫዋቾች መካከል ያሬድ ባዬ፣ ቸርነት ጉግሳና ሀብታሙ ታደሰን በመቀነስ የመጨረሻ 23 ተጫዋቾችን ትናንት ይፋ አድርገዋል።

ብሄራዊ ቡድኑ ትላንት የመጨረሻ የአገር ቤት ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታዲየም በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱ ተገልጿል፡፡

ተጫዋቾችን ጨምሮ 33 የልዑካን ቡድን አባላት ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ጊኒ ቢሳው ጉዞ ማድረግ የጀመረ ሲሆን ቡድኑ በቶጎ መዲና ሎሜ በኩል በማድረግ ማምሻውን ቢሳው ከተማ እንደሚገባ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በ “ስታዲዮ ዲ ሴቴምብሮ” ሜዳ ይከናወናል።

ዋልያዎቹ ከጊኒ ቢሳው ጋር ከተጫወቱ በኋላ ከጅቡቲ ጋር ሰኔ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚያደርጉት የማጣሪያ ጨዋታ ወደ ሞሮኮ የሚያቀኑ ይሆናል።

በተያዘው ሳምንት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ አህጉራት የሚካሄዱ ሲሆን በአፍሪካም ከፊታችን ረቡዕ ጀምሮ ይከናወናል።

45 ሀገራት በዘጠኝ ምድብ ተከፍለው በሚያደርጉት የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ኢትዮጵያ በምድብ 1 ከግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳውና ጅቡቲ ጋር ተደልድላለች።

ኢትዮጵያ እስከ አሁን በምድቧ ባደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች በቡርኪናፋሶ 3 ለ 0 ስትሸነፍ ከሴራሊዮን ጋር ያለምንም ግብ አቻ ተለያይታ በ1 ነጥብ በምድቡ 5ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

23ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ፣ካናዳና ሜክሲኮ ጣምራ አዘጋጅነት እ.አ.አ በ2026 የሚካሄድ ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 አገራት ይሳተፋሉ።

አፍሪካም በዓለም ዋንጫ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 9 አገራት የምታሳትፍ ሲሆን በተጨማሪም አንድ አገር በሌላ አህጉር ከሚገኝ አገር ጋር የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አድርጎ ካሸነፈ አህጉሪቷን ወክሎ የሚሳተፍ ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም