በኢትዮጵያ ባህላዊ የፍትህ አሰጣጥ ሥርዓትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው - የፍትሕ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ባህላዊ የፍትህ አሰጣጥ ሥርዓትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው - የፍትሕ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 26/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባህላዊ የፍትህ አሰጣጥ ሥርዓትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ተናገሩ።
"ማኅበረሰብ አቀፍ የፍትህ አገልግሎት ሚና በኢትዮጵያ የፍትህ ዘርፍ" በሚል መሪ ኃሳብ የባለድርሻ አካላት ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፌዴራልና ክልል የፍትሕ ዘርፍ አመራሮች እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ተገኝተዋል።
የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባህላዊ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓትን አለመግባባቶችና ግጭቶችን ለመፍታትና የተረጋጋ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ወሳኝ ናቸው።
በተጨማሪም ባህላዊ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓቱ የፍትህ አሰጣጡን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ አገልግሎቱን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም ባህላዊ የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓት በጥናትና ምርምር ይበልጥ በማጎልበት ሥራ ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ፍትሕን ለማስፈን የተቋቋሙ ፍርድ ቤቶች ከሰው ኃይል፣ መሰረተ-ልማትና ሌሎች ችግሮች አኳያ በቂ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም ብለዋል።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
በተለይም አገልግሎት ፈላጊው በቋንቋው በእሴቱና ባህሉ እንዲዳኝ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ሚና የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በአቅም መገንባት እንዲሁም በሰው ኃይል ማጠናከር ጉዳይ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል ነው ያሉት።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ዘርፉን ለማጠናከር በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የድርሻውን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ላይ የሲዳማ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት "አፊኒ" በተሞክሮነት የሚቀርብ ሲሆን፤ ውይይት እንደሚደረግበትም ተገልጿል።