ቀጥታ፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮሪያ ሪፐብሊክ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ነው - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/2016(ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሪያ ሪፐብሊክ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር እድል የሚፈጥር መሆኑን በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኮሪያ ሪፐብሊክ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።

በዛሬው እለትም ከኮሪያ ሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ይኦል ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት ተወያይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጉብኝት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ፤ ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኮሪያ ሪፐብሊክ የቆየና ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ወዳጆች ሀገራት መሆናቸውንም አምባሳደሩ አስታውሰዋል።


 

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአሁኑ ጉብኝትም አዳዲስ የትብብር ግንኙነቶችን ለመፍጠርና የቆየውን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

የፋይናንስ ትብብርን ጨምሮ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ፣ የግብርና ልማትና ሌሎችም መስኮች ሁለቱ ሀገራት ይበልጥ ተቀራርበው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እና የኮሪያ ሪፐብሊክን የህዝብ ለህዝብ ትስስር፣ የባህል፣ የትምህርትና በቱሪዝም መስክ ትብብሩን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም አምባሳደር ደሴ ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም