በምክክር ሂደቱ ለሀገር የሚበጁ ጥልቅ ሃሳቦችን በማንሳት ታሪካዊ አሻራችንን እያኖርን ነው - የባለድርሻ አካላት ተወካዮች - ኢዜአ አማርኛ
በምክክር ሂደቱ ለሀገር የሚበጁ ጥልቅ ሃሳቦችን በማንሳት ታሪካዊ አሻራችንን እያኖርን ነው - የባለድርሻ አካላት ተወካዮች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/2016(ኢዜአ)፦ በምክክር ሂደቱ ለሀገር የሚበጁ አካታችና ጥልቅ ሃሳቦችን በማንሳት ታሪካዊ አሻራቸውን አያኖሩ መሆኑን በአጀንዳ ልየታ ላይ እየተሳተፉ ያሉ የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ገለጹ።
አዲስ አበባን ወክለው አጀንዳ የሚሰጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአጀንዳቸው ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡
በውይይቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ወክለው የተመረጡ 121 የህብረተሰብ ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሶስቱ የመንግስት አካላት ተወካዮች፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎችም እየተሳተፉ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲ፣ የማህበራት፣ ተጽእኖ ፈጣሪዎችና የመንግስት አካላት ተወካዮችን የምክክሩን ሂደት በማስመልከት ኢዜአ አነጋግሯቸዋል።
የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ተወካዮች ምክክር በአጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ በማደራጀት፣ በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ በዴሞክራሲያዊ እና መርሆችን ባከበረ መልኩ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሄ ለማፈላለግ በሚደረገው ጥረት የአጀንዳ ሃሰቦችን በመቅረጽ ረገድ ጠንካራ ተሳትፎና ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከቀድሞው ሰራዊት ድጋፍና ልማት ማህበር የተወከሉት ኮሎኔል አድማሱ ብርሃኑ፤ የምክክር ሂደቱ ከምንም በላይ የሀገርን ጥቅም ዘላቂ ሰላምና ህልውና ያስቀደመ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በዚህ ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ በሀገሬ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የመምከር እድል በማግኘቴ ትልቅ ክብርና ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
በምክክሩ እየተሳተፉ ከሚገኙት ታዋቂ ግለሰቦች መካከል ተሻለ ሰብሮ (ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክሩ የዘመናት ጥያቄዎችን በመመለስ የኢትዮጵያን ሰላም በጠንካራ መሰረት ላይ የሚያኖር መሆኑን ገልጸዋል።
የምክክር ሂደቱ በመደማመጥና በመከባበር የቀጠለው የአጀንዳ ልየታ ላይ ያተኮረው ውይይትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ አንድነት፣ ብሔረዊ መግባባት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት ምክክሩ ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ለፍትህ ፓርቲ የተወከሉት መሃመድ አብራር፤ የኢትዮጵያ ችግሮች በውይይት የሚፈቱበት ልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ ደርሰናል ብለዋል።
በመሆኑም ምክክሩ በሰከነ መንፈስ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ይዞ የመጣውን እድል ሁላችንም ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
ከመንግስት አካል ከአዲስ አበባ ምክር ቤት ተወካዮች መካከል ዘይነባ ሽኩር፤ የአጀንዳ መለየት የምክክር መድረኩ በነፃነትና አሳታፊ በሆነ መልኩ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው፤ በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት አጀንዳዎችን በነፃነት በመለየት ምክክራቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።