ቋሚ ኮሚቴው በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ቋሚ ኮሚቴው በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገለጸ
ሶዶ፤ ግንቦት 25/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በወላይታ ሶዶ ከተማ እያከናወነ የሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክት ተስፋ ሰጪ መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው የመንገድ ፕሮጀክቱ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ በመስክ በመመልከት ገምግሟል።
በዚህ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጋሻላው ገላ እንደተናገሩት፤ የከተማው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ እንቅስቃሴ መልካም ነው።
በፌዴራል መንግስት የሚሰሩና በሀገሪቱ ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ቋሚ ኮሚቴው እየተመለከተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሶዶ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የመንገድ ፕሮጀክት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ለከተማው እድገትና ለህዝቡ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሶዶ አካባቢ ፕሮጀክቶች ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሰለሞን ሞላ፤ በወላይታ፣ በከምባታ፣ ሀዲያ፣ ጎፋና ጋሞ ዞኖች ውስጥ በመንገዶች አስተዳደር የተጀመሩ 13 የመንገድ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከነዚህም የሶዶ ከተማ የመንገድ ፕሮጀክት 13 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ጠቅሰው፤ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በከተማው ከሌዊ ሪዞርት እስከ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ እንዲሁም ከአረካ ከተማ መገንጠያ እስከ ጉኑኖ ከተማ ማዞሪያ ያለ መሆኑ ተጠቅሷል።