ቀጥታ፡

የውጭ አገር ህጋዊ የሥራ ስምሪትን ከመካከለኛው ምስራቅ በተጨማሪ ወደ አውሮፓና ኤስያ ለማስፋት እየተሰራ ነው - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ግንቦት 25/2016(ኢዜአ)፦ የውጭ አገር ህጋዊ የሥራ ስምሪትን ከመካከለኛው ምስራቅ በተጨማሪ ወደ አውሮፓና ኤስያ አገራት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

በህጋዊ መልኩ የምናሰማራባቸውን አገራት በየጊዜው የምናሳውቅ በመሆኑ ዜጎች በአጭበርባዎች እንዳይታለሉ ሲሉም መክረዋል።

የውጭ አገራት የስራ ስምሪትን በሚመለከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል፤ከአገራት ጋር ህጋዊ የሥራ ስምሪት ስምምነት በማድረግ የሰለጠነ የሰው ሃይል ስምሪት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በውጭ አገራት የሥራ ስምሪት የዜጎችን መብት፣ ክብርና ደኅንነት በማስጠበቅ የተሻለ ክፍያና የአሰሪ ግንኙነት እንዲፈጠር እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።  

በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ከመካከለኛው ምስራቅ በተጨማሪ ወደ አውሮፓና ኤስያ ገበያም እየተገባ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በአስር ወራት ብቻ 304 ሺህ ዜጎች ስምምነት ወደተደረሰባቸው አገራት የሥራ ስምሪት ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

በየሀገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ለዜጎች የቅርብ ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ገልጸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የስራ ስምሪት ህጋዊ ስምምነት ባልተደረገባቸው አገራት "ለሥራ እንልካለን" የሚሉ ህገ-ወጥ አዘዋዋሪና አጭበርባሪዎች በመኖራቸው ዜጎች አንዳይታለሉም መክረዋል።

በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ አካላት ላይ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ዜጎችም ለሚኒስቴሩና ለህግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። 

ዜጎችም በተቋሙ የማህበራዊ የትስስር ገጽ ላይ በመግባት ህጋዊ የሥራ ስምሪት ሰጪ ኤጀንሲና ተቀባይ ሀገራትን በማረጋገጥ ከህገወጥ አዘዋዋሪዎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ አስገንዝበዋል።

የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያመለክተው እስካሁን ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ጆርዳን እና ኳታር ህጋዊ የሥራ ስምሪት እየተሰጠባቸው ይገኛል።

በቅርቡም ከቤሩት እና ኩዌት ጋር የሥራ ስምሪት ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም