ቀጥታ፡

ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ ረገድ የተጀመረው ሀገር አቀፍ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ

ድሬደዋ ፤ግንቦት 25/2016 (ኢዜአ)፡- ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ በራስ አቅም የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ የተጀመረው አገር አቀፍ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ተናገሩ።

በድሬዳዋ የታክስ ህግን አክብረው በታማኝነት ግብራቸውን ለሚከፍሉ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ትናንት ምሽት ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።

ለአራተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚሁ ሥነሥርዓት ላይ ተገኝተው ዕውቅናና ሽልማቱን የሰጡት የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ እንደተናገሩት፤ እንደ አገር ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ ለመሰብሰብ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች አበረታች ናቸው። 

በአገር አቀፍ ደረጃ አምና 450 ቢሊዮን ብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ 529 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ በትጋት እየተሰራ መሆኑን በአብነት በማንሳት። 

ገቢን በሙሉ አቅም በመሰብሰብ ፍትሃዊ  የማህበራዊ እና የምጣኔ ሃብት ዕድገት ለማስመዝገብና የብልፅግና ጉዞን ዕውን ለማድረግ የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የዜጎችን መሠረታዊ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በፍትሃዊነት ለመመለስ ደግሞ ገቢን አሟጦ መሰብሰብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው መሆኑን በማስገንዘብ።

ወይዘሮ አይናለም እንዳሉት ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ ህገ ወጥ ተግባራትን መከላከል፤ የታክስ መሠረቶችን ማስፋትና በአግባቡ መተግበር እንዲሁም የታክስ ማሻሻያዎች መፈጸም ቅድሚያ ሊሰሩ የሚገቧቸው ናቸው።

በ2017 ዓ.ም ትልቅ የገቢ ዕቅድ ሰንቀን ትልቅ አፈፃፃም ለማስመዝገብ ተዘጋጅተናል ሲሉም ተናግረዋል።

ወይዘሮ አይናለም በድሬዳዋም ለታክስ ህግ እና ለመንግስት አሠራር በመገዛት በታማኝነት ግብርን በመከፈል የአገር ብልፅግና ዕውን እንዲሆን የድርሻቸውን የተወጡትን ተሸላሚ ግብር ከፋዮች አመስግነዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው የታክስ ህግን አክብረው በታማኝነት ግብር እየከፈሉ የሚገኙትንና በየዘርፉ የተሰማሩ ተሸላሚዎችን አመስግነው፤ ግብርን በትክክል መክፈል የአገርና የድሬዳዋን ከፍታ ማረጋገጥ መሆኑን ገልፀዋል። 

በአስተዳደሩ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለመሰብሰብ ርብርብ ይደረጋል ያሉት ከንቲባው፤ አስተዳደሩ በየደረጃው ከሚገኙ ግብር ከፋዮች ጋር ያለውን ትስስር ይበልጥ ያጠናክራልም ብለዋል። 

በአስተዳደሩ የሚሰበሰበው የገቢ መጠን ከዓመት ዓመት እየጨመረ ይገኛል ያሉት ደግሞ የድሬዳዋ የገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም መሐመድ ናቸው።

አምና በአስተዳደሩ ደረጃ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ገቢ የተሰበሰበ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል።

መስሪያ ቤቱ የሚፈልገውን የውጤት ለውጥ ለማምጣት በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ አሠራሮች በመዘርጋት በትጋት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዕውቅናና ሽልማት ከተበረከተላቸው መካከል የስራ ተቋራጭ የሆኑት ኢንጂነር መላኩ ተስፋዬ እና የሆቴል ባለቤት ኖላዊ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ሽልማቱ የበለጠ  ታማኝነታቸውን አፅንተው አገርን ለማሳደግ እንዲሰሩ አነቃቅቷቸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም