ቀጥታ፡

ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ ኢንተርፕርነሮች ተኪ ምርቶችን ማምረት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዳማ፤ ግንቦት 25/2016(ኢዜአ)፦ ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ ኢንተርፕርነሮች ተኪ ምርቶችን በማምረት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ የኦሮሚያ ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ኤባ ገርባ አስገነዘቡ።

በክልሉ ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሻገሩ 1ሺህ 182 አንቀሳቃሾች በአዋጭ የቢዝነስ ዕቅድ ዝግጅት፣ በአዳዲስ የገበያ ሐሳቦችና በኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ላይ የተሰጣቸው ስልጠና ተጠናቋል።

የኦሮሚያ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ኤባ ገርባ ስለ ስልጠናው ዓላማ ሲገልጹ አንቀሳቃሾችን በኢንተርፕርነርሽፕ በማደራጀትና አቅማቸውን በመገንባት በተሻለ ኢንቨስትመንት ተሰማርተው ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል  ነው ብለዋል።

ከጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች ወደ መካከለኛ ባለሀብት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች በተለይም በማኑፋክቸሪንግና ኢንዱስትሪ ዘርፍ በመሰማራት ተኪ ምርቶች ማምረት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ከወዲሁ የኢንተርፕርነርሽፕ ክህሎትና ግንዛቤ እንዲያገኙ ነው ብለዋል።

የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙን ማሳካት የምንችለው አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳብ፣ ፈጠራና ሙያዊ ክህሎት ያላቸውን ኢንተርፕርነሮች የወቅቱ ገበያ ላይ ተመስርተን በጥራትና በብዛት ማፍራት ስንችል ነው ብለዋል።

በዚህም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጨምሮ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲያመርቱ ኢንተርፕርነሮች በክህሎትና ዕውቀት ራሳቸውን ከማብቃት ባለፈ ለሚያመርቱት ምርት ጥራት፣ ተወዳዳሪነትና የገበያ ተደራሽነት ላይ መስራት የሚያስችላቸውን አቅም እንዲፈጥሩ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንተርፕራይዞች በተሸጋገሩበት የኢንቨስትመንት መስኮች ለተሻለ ለውጥ ራሳቸውን እንዲያበቁ ያለመ ገበያና ሙያ መር የክህሎት ስልጠና መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በየወረዳዎቹ በተሰማሩበት የስራ መስኮች ውጤታማ በመሆን ባስመዘገቡት ካፒታልና በፈጠሩት የስራ ዕድል የተመረጡ 1ሺህ 182 አንቀሳቃሾች የኢንተርፕርነርሽፕ የክህሎት ስልጠና ወስደው ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት መሻገራቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

 

የኦሮሚያ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ አህመድ እንዲሪስ በበኩላቸው የክልሉን የኢንቨስትመንት ዕድገት ለማፋጠን ኢንተርፕርነሮችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክህሎት የዳበረና ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ሃይል የማፍራት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ ወደ መካከለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ አንቀሳቃሾች የወሰዱትን የኢንተርፕርነርሽፕ ስልጠና በመጠቀም አዋጭ የሆነና የወቅቱን የገበያ ፍላጎት ያገናዘበ የቢዝነስ ዕቅድ አዘጋጅተው ለቢሮው እንዲያቀርቡም አስገንዝበዋል።

የሚያቀርቡትን የቢዝነስ ዕቅዳቸውን በመገምገም ጥራትና ፈጠራ የታከለበት ገበያና የውድድር ሀሳቦች  ተገቢውን የፋይናንስ፣ የመሬትና የሊዝ ማሽን ድጋፍ በማድረግ ፈጥነው ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገቡ ቢሮው ዕገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ለዚህም ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የክልሉ የሊዝ ማሽን ካፒታል አቅምን በማሳደግ ተገቢው ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሐሰን ሁሴን እንደገለፁት ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የቢዝነስና የፈጠራ ሐሳቦች ያላቸውን ኢንተርፕራይዞች በፋይናንስና በገበያ ልማት ክህሎት ስልጠና እየደገፈ ይገኛል ነው ያሉት።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞችና አንቀሳቃሾች ብድር መሰጠቱን ገልጸው፤ በዚህም ከ55 ሺህ በላይ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችና ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ ከ3ሺህ በላይ ወደ መካክለኛ ባለሀብትነት የተሸጋገሩ አንቀሳቃሾች የኢንተርፕርነርሽፕ የቢዝነስና ገበያ ልማት ስልጠና መውሰዳቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም