በሀረሪ ክልል በቅዳሜ ገበያ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ ክልል በቅዳሜ ገበያ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/2016(ኢዜአ)፦ በክልሉ በቅዳሜ ገበያ አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እየቀረበ መሆኑን የሀረሪ ክልል ንግድ ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ሸሪፍ ሙሜ እንዳሉት በክልሉ የበጋ መስኖ ልማት ስራ በሰፊው በመሰራቱ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረበ ይገኛል።
እየተስተዋለ የሚገኘው የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እና ጤናማ የግብይት ስርዓት እንዲፈጠር እያስቻለ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።
ይህም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍል ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ያለበትን ጫና በመቀነስ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘው የቅዳሜ ገበያ የደላሎችን ሰንሰለት በማስቀረት አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ እንዲገናኝ አድርጓል ብለዋል።
በቅዳሜ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ከመደበኛው ገበያ በተሻለ ዋጋ እየተሸጡ መሆኑን ሸማቾች መግለጻቸውንና ይህም የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል እንደሚያግዝ መጠቆማቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በቅዳሜ ገበያው የተለያዩ የአትክልትና የፍራፍሬ እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማግኘታቸው መደሰታቸውን መናገራቸውም ተጠቅሷል።