የጽዱ ኢትዮጵያ ኑሮ በጤና ንቅናቄ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ትልቅ እገዛ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 25/2016(ኢዜአ)፦ የጽዱ ኢትዮጵያ ኑሮ በጤና ንቅናቄ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ትልቅ እገዛ ያደርጋል።

በኢትዮጵያ ከንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዞ በሚመጡ በሽታዎች በርካታ ሰዎች ለጤና እክል ይዳረጋሉ።

እነዚህ በሽታዎች ከሰው ወደ ሰው በቀላሉና በፍጥነት የሚዛመቱ በመሆኑ ወረርሽኝ የማስከተል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

የአካባቢ ንጽህና ጤናማ ዜጋ ከማፍራት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳለው የጤና ባለሙያዎች ያነሳሉ።

በየካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ የህክምና ጥራት ስፔሻሊስት ዶክተር አብዮት አለሙ በመኖሪያ ቤት አካባቢ የሚከማቹ ቆሻሻዎች ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት ናቸው።

የኮሌራና አተት ወረርሽኝን ጨምሮ አብዛኞቹ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ከአካባቢ ንጽህና ጉድለት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

አይጥና ዝንብን ጨምሮ በሽታ ተሸካሚ ፍጥረታት ንጽህና የጎደለው አካባቢ ለመራባት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል።

ትራኮማ፣ አስምና የሳምባ ምችን ጨምሮ ሌሎች የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ከግልና ከአካባቢ ንጽህና ጉድለት የሚመጡ ናቸው ብለዋል።

የአካባቢ ንጽህና ጉድለት ተላላፊ በሽታዎችን ከማስከተሉ ባለፈ የስነ-ልቦና ጉዳት እንዳለውም ዶክተር አብዮት አብራርተዋል።

የጤና ተቋማትን ጨምሮ በየአካባቢው የሚስተዋለውን የመጸዳጃ ቤት እጥረት ለመፍታት የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ትልቅ ሚና እንዳለውም ነው የገለጹት።

ዜጎች የመጸዳጃ ቤትን በአቅራቢያቸው ማግኘት ከቻሉ ሽንት ለረጅም ሰዓት በመያዝ ምክንያት ለሚከሰቱ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድላቸው ዝቅተኛ እንደሚሆን ነው ያነሱት።

ጽዱ ኢትዮጵያ ኑሮ በጤና ንቅናቄ ኢትዮጵያ የምትከተለውን በሽታን አስቀድሞ የመከላከል ፖሊሲ ያግዛል ብለዋል።

የግልና የአካባቢ ንጽህና ጤናን ከመጠበቅ ጋር ያለውን ቁርኝት ለህብረተሰቡ በማሳወቅ በኩል የጤና ባለሙያዎች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አንስተዋል።

የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄን በየወረዳው ያሉ የጤና ተቋማት በበላይነት ይዘው ለውጤታማነቱ ሊሰሩ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የግልና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ የኢትዮጵያውያን ባህል እንዲሆን ንቅናቄው ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም