የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትና ካሳ የሚከፈልበትን ለመወሰን የወጣው የአዋጅ ማሻሻያ የክልሎችን በጀት ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 24/2016 (ኢዜአ)፦የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ለመወሰን የወጣው የአዋጅ ማሻሻያ የክልሎችን በጀትና ፍትኃዊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባ ተመላከተ። 

ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ለመወሰን የወጣው አዋጅ 1161/2011 ማሻሻያ ላይ ከክልል ምክር ቤቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

በነባሩ አዋጅ የመሰረተ ልማት ገንቢው ለልማት ተነሺዎች የካሳ ክፍያ እንዲከፍልና የወሰን ማስከበር ሥራዎችን እንዲያከናውን መደረጉ አላስፈላጊ የሥራ ጫናና የጊዜ ብክነት ማስከተሉ አዋጁን ማሻሻል ካስፈለገባቸው ገፊ ምክንያቶች ተጠቅሷል።

የፌዴራል ተቋማትን የመሰረተ ልማት ግንባታ የካሳ ክፍያ የፌዴራል መንግሥት የሚሸፍን መሆኑን ባልተገባ መንገድ በመረዳት ያልተገባ የካሳ ክፍያ ግመታና ሌሎችም ገፊ ምክንያቶች አዋጁን ለማሻሻል መነሻ መሆናቸውም ተገልጿል።  

በተለይም በክልሎችና በፌዴራል ተቋማት መካካል የተቀናጀ አሰራር ባለመኖሩ የተጋነኑ የካሳ ይገባኛል ጥያቄዎች እንዲነሱና ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዳይጠናቀቁ ማድረጉም አንዱ የአዋጁ ክፍተት ነበር ተብሏል። 

ይህንንም ተከትሎ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበትና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ለመወሰን የመጣው አዋጅ ማሻሻያ ተደርጎበታል። 

በአዋጁ ማሻሻያ እንደተመላከተው፣ የፌዴራል መንግሥት ለሚያከናውናቸው የልማትና የማኅበራዊ አገልግሎት ማስፋፊያ ግንባታዎች ንብረት የመገመት የመክፈልና የማስነሳት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ለክልልና ከተማ አስተዳደሮች ተሰጥቷል።

ይሁንና የማሻሻያ አዋጁን አስመልክቶ በተደረገው ውይይት የተሳተፉ የተለያዩ ክልሎች አፈ-ጉባኤዎችና ባለድርሻ አካላት ማሻሻያው የክልሎችን በጀትና ፍትኃዊ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ታሳቢ ያላደረገ ነው ብለውታል።

በነባሩ አዋጅ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት አማራጭ መፍትሔዎችን መፈለግ እንጂ የካሳ ክፍያውን ክልሎች ላይ መጣል ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።


 

የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው በነባሩ አዋጅ ላይ መሬቱን የሚያስተዳድረው አካል ሌላ ሆኖ የመሰረተ ልማት የሚዘረጋው የፌደራል መንግሥት የካሳ ክፍያውን እንዲከፍል መደረጉ ሕጋዊ ሥርዓትን ያልተከተለ ነው ብለዋል።

በአዋጅ ማሻሻያው የተመላከተው፤ ንብረት የመገመት የመክፈልና የማስነሳት ሥራ ሙሉ ለሙሉ ለክልልና ከተማ አስተዳደሮች መሰጠቱ  የፕሮጀክቶችን የመፈጸም አቅም ለማሻሻልና የቅንጅት አሰራርን ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።

የአዋጁ መሻሻል በፌዴራል መንግሥቱ ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የካሳ ክፍያ ጉዳይ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች መጓተት ብቸኛው መንስኤ ባይሆንም ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ የተሻሻለው አዋጅ ይህንን ችግር በማስቀረት ሁነኛ መፍትሄ እንደሆነ ነው ያብራሩት።  

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮችና የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በግልና በጋራ ውይይት ያደረጉበት ሲሆን ከተለያዩ አካላትም ግብዓት እያሰባሰቡ ይገኛሉ።

የዛሬው የባለድርሻ አካላት ውይይትም  ለ4ኛ ጊዜ የተደረገ ሲሆን የመጨረሻ የግብዓት ማሰባሰቢያ እንደሆነ በምክር ቤቱ የከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸዊት ሻንካ ገልጸው ነበር። 

ይሁንና የውይይቱ ተሳታፊዎች በማሻሻያ አዋጁ ላይ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃሳብና አስተያየት ሊታከልበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም