መንግሥት የወደብ አማራጮችን ለማስፋት የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የወደብ አማራጮችን ለማስፋት የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016 (ኢዜአ)፦የአገሪቱን የአሁንና ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ እድገት ታሳቢ በማድረግ መንግሥት የወደብ አማራጮችን ለማስፋት የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተመላከተ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ሎጀስቲክስ ዘርፍ ማኅበር ጋር በመተባበር በወደብ አማራጭ ስትራቴጂ ፈተናዎችና እድሎች ዙሪያ የፓናል ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሁሩ ብርሃኑ ደኑ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ወደብ ለአንድ አገር የገቢና የወጪ ንግድ መሳለጥ ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት በዋናነት የጂቡቲ ወደብን በኪራይ ስትጠቀም መቆየቷን አንስተዋል አሁን ላይ የወደብ አማራጯን ማስፋት እንዳለባት ተናግረዋል።
በተለይም አገሪቱ አሁን ላይ እያስመዘገበች ካላው እድገትና የወጪ ገቢ ንግድ እየጨመረ ከመምጣቱ አኳያ ተጨማሪ ወደብ ያስፈልጋታል ነው ያሉት።
ለአብነትም በ1980ዎቹ ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልከውና የምታስገባው የሸቀጦች መጠን ከ1 ሚሊየን ቶን ያልበለጠ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ይህ አሃዝ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን አመላክተዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ ተጨማሪ ወደቦችን መጠቀም ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከተለው ያለው የወደብ አማራጮችን የማስፋት ስትራተጂ ወቅታዊና የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ የወደብ አማራጮችን የማስፋት እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አገራትም የራሱ ጥቅም እንዳለው አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማቲዎስ ኢንሰርሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ቁጥር አንጻር ተጨማሪ ወደቦችን መጠቀም እንደሚያስፈልጋት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባላት መርከብና የሎጂስቲክ አቅም የቀጠናው አገራትን ጭነት በማመላለስ ጭምር የንግድ እንቅስቃሴው እንዲሳለጥ እያደረገች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ባህር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሲራጅ አብዱላሂ ናቸው።
ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቿን ከዚህ በላይ ብታሰፋ አጠቃላይ የቀጣናው ንግድ ለማሳለጥ የሚያስችል አቅም እንደምትፈጥር ተናግረዋል።
በዘርፉ የሚሰራው ኤል-ቲ-ኦ ድርጅት ተጠባባቂ ዳይሬክተር ተመስገን ይሁኔ፤ መንግሥት እያከናወናቸው ያሉ የወደብ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች አበረታች መሆናቸውን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ሎጀስቲክስና የዘርፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት ኤልሳቤት ጌታሁን፤ አማራጭ ወደቦችን መጠቀም ተወዳዳሪነትን የሚያጠናክርና የንግድ ልውውጥን የሚያቀላጥፍ በመሆኑ ወደብ የማስፋት እንቅስቃሴው የግሉ ዘርፍ ሊደግፈው እንደሚገባ አመላክተዋል።