ቀጥታ፡

እግር ኳስ የህዝቦች አብሮነት እንዲጎለብት የሚያደርገውን እሴት ከፍ አድርጎ ለመጠቀም ዘርፉን ማጠናከር ይገባል-አቶ ኢሳያስ ጅራ

ሚዛን አማን/ሀላባ ቁሊቶ  ፤ ግንቦት 24/2016(ኢዜአ)፦ እግር ኳስ  የሕዝቦች አብሮነት እንዲጎለብት የሚያደርገውን እሴት ከፍ አድርጎ ለመጠቀም ዘርፉን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ አስገነዘቡ ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የ2016 እግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ዛሬ በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።

በማጠቃለያ ስነ ስርአት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንደገለጹት እግር ኳስ ሕዝቦችን የሚያፋቅር ትልቅ የስፖርት ዘርፍ ነው።

"ስፖርቱ ከማሸነፍና መሸነፍ ባለፈ የህዝቦች አብሮነት እንዲጎለብት የሚያደርገውን እሴት ከፍ አድርጎ ለመጠቀም ዘርፉን ማጠናከር ይገባል" ብለዋል።

"በየአካባቢው ያሉ አቅሞችን ለመጠቀም የሚደረጉ ጥረቶችን በመደገፍ ተፎካካሪ ስፖርተኞች እንዲወጡና ዘርፉ ለአብሮነትና ለሰላም ግንባታ መጠናከር ያለውን አቅም ለመጠቀም እንሰራለን" ሲሉም አክለዋል።

ክልሉ ለእግር ኳስ ትኩረት ሰጥቶ የማደራጀትና የማብቃት ሥራ እየሠራ በመሆኑ አመስግነው በቀጣይ የክልሉን እግር ኳስ ለማጠናከር በቅንጅት እንደሚሰራ አቶ ኢሳያስ አመላክተዋል።

በውድድሩ18 የእግር ኳስ ክለቦች መሳተፋቸውን የገለጹት ደግሞ  የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትልና የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አህመዲን አወል ናቸው።

ውድድሩ ወንድማማችነት ጎልቶ የታየበት መሆኑን ገልጸው ብቃት ያላቸውን ክለቦች ለመፍጠር ቢሮው ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ አመልክተዋል።

በማጠቃለያው ስነ ስርአት ለፍጻሜ የደረሱ የጌሻና ጊምቦ ዳዲበን የእግር ኳስ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታ ጌሻ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት  በማሸነፍ የሻምፒዮናው ዋንጫ ባለቤት ሆኗል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለክልሉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን 250 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው ኳሶችን በስነ ስርአቱ ላይ  በስጦታ አበርክቷል።

በሌላ በኩል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእግር ኳስ ክለቦች ሻምፒዮና ውድደር በሀላባ ቁሊቶ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።

ውድድሩ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚኖር ውድድር ክልሉን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ማፍራትን አላማ ያደረገ መሆኑን የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ሰርካለም ሳሙኤል ተናግረዋል።

በተጨማሪም ስፖርት ለማህበራዊ መስተጋብር እንዲሁም ለህዝብች አብሮነት፣ትስስርና ለወዳጅነት ያለውን ፋይዳ ለማጠናከርና ለመጠቀም እንደሆነም አመልክተዋል።

የሻምፒዮና ውድድሩ በ22 የእግር ኳስ ክለቦች መካከል እንደሚካሄድና ለ17 ቀናት  እንደሚቆይ አስታውቀዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም