ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾችና አሰልጣኞችን አጠቃላይ ዓመታዊ ክፍያ የሚቆጣጠር ኮሚቴ ተዋቀረ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ለተጫዋቾችና አሰልጣኞች የሚከፍሉትን ዓመታዊ ጥቅል ክፍያ የሚቆጣጠር ኮሚቴ መዋቀሩን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።

የወጪ ገደቡ የክለቦችን የፋይናንስ አስተዳደር ጤናማ የማድረግ ጠቃሜታ እንዳለውም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ችግሮችን የተመለከተ ጥናት ከሁለት ዓመት በፊት ማስጠናቱ የሚታወስ ነው።

ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይህ ጥናት የክለቦች አወቃቀር፣ የክለቦች የፋይናንስ ሁኔታ፣ የፕሪሚየር ሊጉን አጠቃላይ ቁመና፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለቦች ጋር ያለውን ግንኙነትና የክለቦች ፈቃድ አሳጠጥ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።

ከጥናቱ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ ክለቦች ያላቸው የፋይናንስ አስተዳደር እንዲሻሻል ምን መደረግ አለበት? የሚለው ላይ ሲሆን ጥናቱን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የክፍያ ሥርዓት አስተዳደር መመሪያ ተዘጋጅቷል። 

ይህ መመሪያ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም ማህበሩ ባካሄደው 4ኛው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ጸድቋል።

በመመሪያው አማካኝነት ክለቦች በዓመት ለተጫዋቾችና ለአሰልጣኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ከ57 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈል አይችሉም። 

የአክሲዮን ማህበሩ ሰብሳቢ ክፍሌ ሰይፈ ጥናቱንና መመሪያውን በተመለከተ  ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከ16ቱ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ውይይት እንዳደረጉበት ገልጸዋል።

በመመሪያው መሰረት የክለቦችን ፋይናንስ ኦዲት የሚያደርገው ድርጅት ከአክሲዮን ማህበሩና ከክለቦቹ ጋር ውል እንደሚፈጽም አመልክተዋል።

ድርጅቱ የክለቦቹን የፋይናንስ ሁኔታ ኦዲት ካደረገ በኋላ ውጤቱን ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኦዲት ሪፖርቱ የሚቀርብለት አካል ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጣ ኮሚቴ መሆኑን ነው ሰብሳቢው የገለጹት።

የተዋቀረው ኮሚቴ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ጠበቆች ማህበር፣ የፌደራል ሒሳብ ባለሙያዎች ማህበር፣ የፌደራል ስነምግባርና የፀረ-ሙስና ኮሚሽንና የፋይናንስ ደህነንት አገልግሎት በውስጡ መያዙን አመልክተዋል።

ኮሚቴው ክለቦች በተቀመጠላቸው የወጪ ገደብ ለተጫዋቾችና ለአሰልጣኞች ዓመታዊ ጥቅል ክፍያ እየከፈሉ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን እንደሚቆጣጠር አስረድተዋል።

መመሪያው ለተጫዋቾችና ለአሰልጣኞች በግል የሚከፈላቸው ክፍያ ላይ ገደብ እንደማያስቀምጥና ዋንኛ ትኩረቱ ዓመታዊ ጥቅል የክለቦች ክፍያ ጣሪያ እንደሆነና ከደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ክፍያ ውጪ በሌሎች ወጪዎች ላይ ገደብ እንደማያስቀምጥ በመጠቆም።

ይህ መመሪያ በእግር ኳሱ ላይ ያለውን የገንዘብ ክፍያ ፍትሐዊ በማድረግና ማጭበርበርን በመከላከል ጤናማ የክለቦች የፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የክፍያ መመሪያውና የጥናት ፎኖተ ካርታው ከ2017 ዓ.ም አንስቶ ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመው ኮሚቴው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል።

ክለቦች ቅሬታ ካላቸው የሚያቀርቡበት ሁኔታ መመቻቸቱንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም