የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዲጅታል ፋይናንሺያል ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከግል ባንኮች ፕሬዝዳንቶች ጋር ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የዲጅታል ፋይናንሺያል ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከግል ባንኮች ፕሬዝዳንቶች፣ ተወካዮች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ከባንኮች ጋር ተያይዘው የሚፈፀሙ የሳይበር፣ የሞባይል ባንኪንግ እና ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚፈፀሙ ወንጀሎች በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰቡና እየተበራከቱ በመምጣታቸው በጋራ ወንጀሉን ለመከላከል የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም የሀገራችን ኢኮኖሚ እና የቴክኖሎጂ አቅም እያደገ ሲሄድ በዚያው ልክ ችግሩም አብሮ እያደገ እንደሚሄድ ታሳቢ መደረግ እንዳለበት አንስተዋል።

ቴክኖሎጂው ሲበለጽግ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ተለይቶ ለደንበኞች፣ ለባንክ ሠራተኞች እና ለሕግ አስከባሪው ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ በአፅንኦት ገልጸዋል።

አክለውም ቴክኖሎጂ ሲበለጽግ ከባንኮች እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ፖሊስም መረጃ የሚያገኝበትና የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል መሳሪያዎችን በመጠቀም በፋይናንሺያል ኢንዱስትሪ ውስጥ የማጭበርበር ድርጊቶችን በሚፈፅሙ ወንጀለኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ እና በባንኮች የአሰራር ሂደት ላይ የነበረው ሚስጥር የመጠበቅ ባህል በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ ዕድገት እየተሸረሸረ መምጣት እንደሌበትም አሳስበዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ በበኩላቸው ዲጂታል ፋይናንሺያል ላይ የሚስተዋለው ወንጀል የሰፋና የገዘፈ ችግር መሆኑን በመገንዘብ ለችግሩ መፍትሄ ማስቀመጥ እንጂ ከዲጂታል ፋይናንስ ሲስተም ውጭ መሆን እንደማይቻል ገልፀዋል፡፡

የዲጅታል ፋይናንስ ወንጀልን ለመከላከል ቴክኖሎጂን፣ የህግ ማዕቀፍ፣ ትብብርና የማህበረሰብ ንቃት ላይ የሚሰራው ስራ ችግሩን እንደሚያቃልል ተናግረው በተጫማሪም ብሄራዊ መታወቂያ (National ID) መጠቀም እንደ አንድ የችግሩ ማቃለያ መፍትሄ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ በሞባይል ባንኪንግና በሶሻል ሚዲያ አማካኝነት በሚፈፀሙ ወንጀሎች ዙሪያ ያዘጋጀውን የጥናት ሰነድ የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ አቅርበው ውይይት መካሄዱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥና በየደረጃው ያሉ የምርመራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በቀጣይም በመድረኩ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን አፈፃፀም ለመገምገም የጋራ ውይይት ፎረሙ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም