በመዲናዋ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች   ምቹ የኑሮ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ  በሥራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረጉን ነው -ተጠቃሚዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 24/2016 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ተገንብተው የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምቹ የኑሮ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ በስራ ዕድልም ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የስራ ዕድል የተፈጠረላቸውና የቤት ዕድለኛ የሆኑ ወገኖች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጎ ፈቃደኛ ባለሀብቶችን በማስተባበር የሚያስገነባቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ ወገኖችን እያስተላለፈ ይገኛል። 

በቅርቡም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ጋር በመተባበር በልደታ ክፍለ ከተማ ያስገነባቸውን የመኖሪያ ቤቶች ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለአቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ ወገኖች አስተላልፈዋል። 

በክፍለ ከተማው ለአቅመ ደካማና አካል ጉዳተኛ ወገኖች የተላለፉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች የእንጀራ መጋገሪያ ፋብሪካ፣ የወንዶች እና የሴቶች የውበት መጠበቂያ፣ የህፃናት ማቆያ፣ ልብስ ስፌትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡና የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ቦታዎች የተካተቱባቸው ናቸው። 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኞችና በአካባቢው የሚኖሩ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች መንግስት ያመቻቸላቸው የስራ እድል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ከመኖሪያ ቤት ዕድለኞች መካከል ወይዘሮ ስንቅነሽ ዝናቡ፤ መንታ ልጆችን እና የጤና እክል ያለበትን ልጃቸውን  ይዘው ምቹ ባልነበረ መኖሪያ ቤት ህይወትን በአስቸጋሪ ሁኔታ ይገፉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከተማ አስተዳደሩ ያስገነባው ምቹ የጋራ መኖሪያ ቤት ዕድለኛ መሆናቸው ህይወትን በተሻለ ሁኔታ መምራት የሚያስችል አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው በታላቅ ደስታና ምስጋና ይናገራሉ። 

የአካባቢው ነዋሪና የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወይዘሮ  ዘሪቱ አስፋውም ምንም አይነት ስራ እንዳልነበራቸው በማስታወስ፤ በአካባቢው በተገነባው የእንጀራ ፋብሪካ የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።




ያገኙት የሥራ ዕድል የተሻለ ህይወት መምራት የሚያስችል መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል። 

ወይዘሮ  ፀሀይ ገብሬ  እንደሚሉትም መስራት እየቻሉ ከአስር ዓመት በላይ ስራ በማጣት የቤት ኪራይና የቤተሰብ ወጪን ለመሸፈን ተቸግረው እንደቆዩ አስታውሰዋል። 


 

በጋራ መኖሪያ ቤቱ አካባቢ በተገነባው የእንጀራ መጋገሪያ ያገኙት የሥራ እድል ቤተሰባቸውን በተሻለ ሁኔታ ለመምራት ከፍተኛ ተስፋ ፈጥሮባቸዋል። 


 

መንግስት በእንጀራ ፋብሪካው ተደራጅተው እንዲሰሩ ባመቻቸላቸው ምቹ  አጋጣሚ  በመጠቀም  ሴቶች  ሰርተው መለወጥ  እንደሚችሉ  ለማሳየት በቆራጥነት እንደሚሰሩ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ሰርካለም አሰፋ ናቸው ። 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም