ቀጥታ፡

ፍርድ ቤቶችና የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽንን በተሟላ መልኩ ለመተግበር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ የፍርድ ቤቶችና የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽንን በተሟላ መልኩ ለመተግበር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ  ገለጹ።

የአገራዊ የፍርድ ቤቶችና የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የ2016 በጀት ዓመት የ9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ተገምግሟል።


 

በመድረኩ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።  

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የፍትህ ዘርፍና የዳኝነት አካሉን ሪፎርም ማድረግ የመንግሥት ትልቁ አጀንዳ ነው።

ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር ብቃት፣ ሥነ-ምግባርና ክህሎት ባለው የሠው ኃይል በማደራጀት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ማዘመን እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዘርፉን የማዘመን ሥራዎች የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው የዘርፉን ትራንስፎርሜሽንን በተሟላ መልኩ ለመተግበር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በጋራ በተቀመጡ አሰራሮች መሰረት አፈጻጸሙን መገምገም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ በበኩላቸው የዘርፉ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም መልካም መሆኑንና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ቅንጅታዊ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ ይበልጥ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፤ ፍርድ ቤቶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲሰጡ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። 

ለዚህም ፍርድ ቤቱ የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው  በቀጣይም የተገኙ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን በማጠናከር ለላቀ ስኬት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። 

የፍትህ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ ወሳኝ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን የማረጋገጥ ሥራ ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው ያሉትን ሃብቶች አሟጦ በመጠቀም መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በአፈጻጸም ላይ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽንን በተሟላ መልኩ ለመተግበር የተከናወኑ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል።

በቀጣዮቹ ጊዜያት የተጀመሩ ውጤቶችን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፤ የተጀመሩ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችንም ለማጠናከር ርብርብ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም