በክልሉ ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልማትን ለማጠናከርና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ከመንግስት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል--አቶ እንዳሻው ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልማትን ለማጠናከርና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ከመንግስት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል--አቶ እንዳሻው ጣሰው
ሆሳዕና፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክልሉን የልማት ጉዞ ለማጠናከርና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ከመንግስት ጋር በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር አባላት ጋር በክልሉ ልማትና ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ አካሂደዋል።
አቶ እንዳሻው በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ፓርቲዎች በቅንጅት መንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ ለክልሉ ልማትና ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ከመንግስት ጋር አብረው መስራት አለባቸው።
"ሁሉም ፓርቲ የሚታገለው ለልማትና ለህዝብ ተጠቃሚነት በመሆኑ የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም ለህዝብ ተጠቃሚነትና ዕድገት እውን መሆን በጋራ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በክልሉ በመንግስትና በህዝብ ቅንጅት እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን መጎብኘታቸውንም አቶ እንዳሻው ገልጸዋል።
የውይይት መድረኩ ዓላማ በክልሉ በሁሉም መስክ በተጀመሩ የልማት ሥራዎችና ጉድለቶች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠርና ለቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑንም አስረድተዋል።
አቶ እንደሻው እንዳሉት፤ ከክልሉ ምስረታ ማግስት ጀምሮ የህዝቡን የሰላም፣ የልማትና የተጠቃሚነት ጥያቄዎች ለመፍታት በተሰሩ ሥራዎች አበረታች ለውጥ ማምጣት ተችሏል።
የክልሉን ሰላም በማጠናከርና ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም ልማትን ለማፋጠን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በክልሉ ሁለንተናዊ የልማት ጉዞን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማደናቀፍ የሚሰሩ አካላትን ከተግባራቸው ለማስቆም በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በሆሳዕና ከተማ የእናት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ሹመቴ የክልሉ መንግስት ሰላምን በማጠናከር ህብረተሰቡ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ባከናወናቸው ሥራዎች የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን መመልከታቸውን አንስተው፤ በዚህም ተጨባጭ ውጤቶች መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ይበልጥ እንዲመለሱ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በህዝብ ተሳትፎ ለሚሰራው የዘላቂ ሰላም ሥራ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በኢንቨስትመንት ስም የሚተላለፉ መሬቶች ለታለመላቸው ዓላማ የማይወሉበት ሁኔታ እንዳለ አስታውሰው፤ "ይህም የክልሉንና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ስለሚጎዳ ማረም ይገባል" ብለዋል።
የዶንጋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ አየለ መከንጎ በበኩላቸው፣ የሚፈለገውን ልማት በማምጣት ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላም የህዝብ ጥያቄ በአግባቡ እንዲመለስ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ እንደ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት ከፍተኛ ሀላፊነት አለብን ብለዋል።
በክልሉ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የልማት ጎዞ እና ሰላምን አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
"በክልሉ ልማትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ውጤቶች መገኘታቸውን አይተናል" ያሉት ደግሞ በሀላባ ዞን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሰብሳቢ አቶ አንዷለም ንብረቴ ናቸው።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በሌሎችም የማህበራዊ ዘርፎች እየታየ ያለው ተስፋ ሰጪ ውጤት ዘላቂ ሆኖ እንዲጠናከርና የህብረተሰቡም ተጠቃሚነት በዘላቂነት እንዲረጋገጥ አስተዋጾቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
ለገበያ ማረጋጋት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ትኩረት መስጠት ይገባል ያሉት ሰብሳቢው፣ ለዚህም የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ላይ የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራሮች ተሳትፈዋል።