ቀጥታ፡

በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች በመጠቀም ያለቀላቸው የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት በስፋት እንዲመረቱ እየተደረገ ነው

ባህር ዳር ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም ያለቀላቸው ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት በስፋት እንዲመረቱ  እየተደረገ  መሆኑን  የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት “የጥጥ፣ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት እሴት ሰንሰለት በአፍሪካ” በሚል ሀሳብ አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።


 

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ እንደገለጹት፤ በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት የስራ እንቅስቃሴ በራስ አቅም አምርቶ ራስን ለመቻል ትልቅ አቅም ሆኗል።

ባለፉት ዓመታት በትንሹ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የውጭ ምንዛሬ በማውጣት የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ምርቶች ሲገቡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ በራስ አቅም በማምረት ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውጤት መገኘቱን ጠቅሰው፤ የአገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን በመጠቀም ያለቀላቸው ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት በስፋት እንዲመረቱ  እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተገኙ ያሉ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠልም በዘርፉ የተገኙ ውጤቶች የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ገልጸዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ስራ ፈጥሮ የሚተገብር ትውልድ የማፍራት ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

በዘርፉ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት ኢንስቲትዩቱ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንስቲትዩቱ አስተምሮ ከሚያስመርቃቸው መካከልም 25 ነጥብ 6 በመቶ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ሌሎች የስራ እድል በመፍጠር እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

ለዘርፉ ልማት የሚያስፈልጉ ዕቃዎችና የኬሚካል እጥረት መኖሩን  ጠቅሰው፤ ለእነዚህ አማራጭ ለማቅረብ የምርምር ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች የስራ እድል በራስ አቅም በመፍጠር የገቢ ምንጭ ከመሆናቸውም ባለፈ ባህላዊ እሴቶችን አጉልቶ በማሳየት የጎላ ድርሻ እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር እሰይ ከበደ ናቸው።

መንግስት "ኢትዮጰያ ታምርት" በሚል ሀሳብ እየተገበረ ያለው ፋብሪካዎችን የማነቃቃትና በራስ አቅም አምርቶ የመጠቀም ተግባር አበረታችና ለኢንዱስትሪዎች እድገት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች ከአገር አልፎ  የአፍሪካውያን ባህል መሰረት ያደረጉ አልባሳትን በማምረት የባህል ትስስር እንዲኖር በማድረግ አስተዋጿቸው የጎላ ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በእውቀትና በክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው አውደ ጥናት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና የፌዴራልና የዘርፉ ከፍተኛ የአመራር አባላት፣ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም