የአፈር ለምነት መጠበቅ የሚያስችሉ ሀገር በቀል የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በስፋት ለመጠቀም ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የአፈር ለምነት መጠበቅ የሚያስችሉ ሀገር በቀል የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በስፋት ለመጠቀም ትኩረት ተሰጥቷል
አዳማ፣ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፡-ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ የአፈር ለምነት መጠበቅ የሚችሉ ሀገር በቀል የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በስፋት ለመጠቀም ትኩረት መሰጠቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
ግብርና ሚኒስቴር ከ'ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን' ጋር በመተባበር በአፈር ለምነትና ጤንነት አጠባበቅ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአዳማ አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትሩን ወክለው የተገኙት አቶ አብዱሰመድ አብዱ ለኢዜአ እንደገለጹት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ የአፈር ለምነት መጠበቅ ይገባል።
በተለይ የአፈር አሲዳማነትን፣ የአፈር መከላትንና መሸርሸርን ለመከላከል የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና ሀገር በቀል የግበርና ግብዓቶችን መጠቀም የላቀ ሚና አለው ብለዋል።
ለዚህም ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሀገር በቀል የግብርና ግብዓቶችንና ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ዘንድ በስፋት ተደራሽ እንዲሆንና አገልግሎት ላይ እንዲውል እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በተወሰኑ የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚገኘው የእርሻ መሬት ለአፈር አሳዳማነት የተጋለጠ በመሆኑ የአፈር ለምነት ለመጠበቅ ሀገር በቀል የምርት ማሳደግያ ግብዓት አጠቃቀም ላይ ትኩረት ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም ኖራ፣ የእንስሳት ፍግ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያና 'ቨርሚ' ኮምፖስት፣ የአስተራራስ ዘዴን ማዘመን ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የ'ሳሳካዋ አፍሪካ አሶሴሽን' የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ፋንታሁን መንግስቱ እንደገለጹት የአፈር ለምነትና ጤንነትን ለመጠበቅ ሀገር በቀል የግብርና ግብዓት ከአፈር ማዳበሪያ ጋር በመጠቀም ይገባል ይላሉ።
በዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት እንዲመረት ወጣቶች፣ ባለሃብቶችና በዘርፉ የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ሊሳተፉበትና በቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ ሰብልና የእንስሳት ተረፈ ምርቶችን፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያን፣ ጥራጥሬ፣ ቅመማቅሞች፣ የአገዳና የብእር እህሎችን በፈረቃ በመዝራት የአፈር ለምነትና ጤንነትን በዘላቂነት መጠበቅ ያስችላል ሲሉም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ላይ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክረን ከመቀጠል ባለፈ ሀገር በቀል የምርት ማሳደጊያ ግብዓት አጠቃቀም ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።