ኢትዮጵያን ጽዱና አረንጓዴ የማድረግ ግብን ለማሳካት ሁሉም ሚናውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ጽዱና አረንጓዴ የማድረግ ግብን ለማሳካት ሁሉም ሚናውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያን ጽዱና አረንጓዴ የማድረግ ግብን ለማሳካት ሁሉም ሚናውን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር ለሁሉም የምትመች፣ ፅዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያን እንዲሁም ውብ ከተሞችን የመፍጠር ዓላማን ያነገቡ ኢኒሼቲቮችን ማስጀመራቸው ይታወቃል።
ከእነዚህም መካከል በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እንዲሁም ሚያዝያ 18/ 2016 ይፋ የሆነው እና "ጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና" በሚል መሪ ሀሳብ የሚተገበረው የጽዱ ኢትዮጵያ ተነሳሽነት ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ የዘንድሮውን የአካባቢ ጥበቃ ቀን በሚመለከት ከሌሎች ተቋማት አመራሮች ጋር በሰጡት መግለጫ፤ ጽዱና አረንጓዴ አካባቢ ለመፍጠር የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለ31ኛ ጊዜ "መሬትን ማገገም፣ በረሃማነትና ድርቅን መቋቋም" በሚል መሪ ሀሳብ ግንቦት 27 እና 28 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ መርኃ ግብሮች እንደሚከበርም ገልጸዋል።
መንግሥት ለሕዝቡ ጤና ምቹና ጽዱ ኢትዮጵያ ለመፍጠር በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ማህበረሰቡ አካባቢውን ከብክለት ለመጠበቅ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት ዋና ዳይሬክተሯ፥ ተቋማትም አካባቢን የማይጎዳ የምርትና አገልግሎት ሂደትን እንዲከተሉ አሳስበዋል።
የበለጸገች፣ ጽዱ እና አረንጓዴ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተጀመሩ ተነሳሽነቶችን ለማሳካት ሁሉም ሚናውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
ተቋማት ብክለት የማይፈጥር አሰራር እንዲከተሉ የግንዛቤ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመው፥ ከህግ ያፈነገጠ ተግባር ላይ ተሰማርተው በሚገኙት ላይም የህግ የማስከበር ስራ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም በበኩላቸው፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት መተግበር የጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአካባቢ መልሶ ማገገም ትልቅ አሰተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ32 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው፤ ይህም ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለደን ልማትና ለከተሞች ውበት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው አንስተዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው ሀገራት አካባቢ ጥበቃ ፋይዳው የላቀ እንደሆነም ጠቁመዋል።
በእስካሁኑ የመርሐ ግብሩ ትግበራ ሀገራዊ የደን ሽፋን እያደገ ነው ያሉት አቶ ከበደ፥ በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ደን 2 ነጥብ 8 ቢሊየን ቶን የካርበን ክምችት እንዳለው ጥናቶችን ዋቢ አድርገው አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ እንዳሉት፥ በመዲናዋ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል እየተሰራ ነው።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ከከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር ውጤት መምጣቱንም ተናግረዋል።
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሞች 30 በመቶ የአረንጓዴ ልማት እንዲኖራቸው የተቀመጠውን መስፈርት ለማሟላት ባለፉት ዓመታት በተደረገው ጥረት የአዲስ አበባ የአረንጓዴ ሽፋን ከ2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 15 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።
የመዲናዋ ወንዞች ከብክለት የጸዱ እንዲሆኑም በወንዝ ዳርቻ ልማት መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የዓለም አካባቢ ጥበቃ ቀን በጽዳት ዘመቻ፣ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ፣ አካባቢ ጥበቃን በተመለከቱ ውይይቶች እንደሚከበርም በመግለጫው ተመላክቷል።