የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከአፍሪካዊያንና ከተቀረው ዓለም ጋር የማስተሳሰር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከአፍሪካዊያንና ከተቀረው ዓለም ጋር የማስተሳሰር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከአፍሪካዊያንና ከተቀረው ዓለም ጋር የማስተሳሰር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ወደ ምዕራባዊቷ የአፍሪካ ሀገር ሴራሊዮን ''ፍሪታውን'' ከተማ አዲስ በረራ ጀምሯል።
በማስጀመሪያው መርኃ ግብር የአየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ መዳረሻውን በየጊዜው እያሰፋ ነው።
በተለይም ደግሞ አየር መንገዱ የፓን አፍሪካኒዝምን እሳቤ በማንገብ የአፍሪካ ሀገራት እርስ በርስ ለማስተሳሰር እየተጋ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዛሬው እለት ወደ ሴራሊዮን ፍሪታውን ከተማ የተጀመረው በረራ የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
ዛሬ ወደ ሴራሊዮን የተጀመረው ይህ በረራ በሳምንት 3 ጊዜ የሚደረግ ሲሆን የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በሳምንት ወደ 7 ጊዜ እንደሚያድግም ገልጸዋል።
በረራው የሴራሊዮን ዜጎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከአፍሪካ ውጭ ወደ እስያ፣ አውሮፓና አሜሪካ የሚያደርጉትንም ጉዞ የሚያሳልጥ ነው ብለዋል።
በቀጣይም አየር መንገዱ አፍሪካን ከአፍሪካዊያንና ከተቀረው ዓለም ጋር የማስተሳሰር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የጠቆሙት።
በኢትዮጵያ የሴራሊዮን አምባሳደር ሃሮልድ ቡንዱ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሴራሊዮን ፍሪታውን በረራ መጀመሩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ያስችላል።
በተለይም ሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን አጋርነት የበለጠ ለማሳደግ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
በዛሬው ዕለትም አየር መንገዱ በረራ የጀመረባት የሴራሊዮን ፍሪታውን ከተማ በአፍሪካ 64ተኛ መዳረሻው መሆኗ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባሉት 147 በላይ አውሮፕላኖች 136 ዓለም አቀፍና 22 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን እየሸፈነ ይገኛል።