በክልሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ተሰጥቷል
ሆሳዕና፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ ለኢዜአ እንደገለጹት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ተግባራዊ ማድረግ ለማህበረሰቡ ቀልጣፋና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።
በመሆኑም በክልሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከወረቀት ንክኪ የጸዳና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመዘርጋት ወደተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አጋዥ መሆኑንም አቶ ሰላሙ ገልጸዋል።
እንደእሳቸው ገለጻ በክልሉ ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ የሰው ሀይል የማብቃትና ሌሎች የዝግጅት ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ።
የቡታጅራ አጠቃላይ እና የወራቤ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በሌሎች ተቋማት የዲጅታል አገልግሎት ተግባራዊ የማድረግ ሥራ መጀመሩንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ቴክኖሎጂውን ቀደም ብለው ተግባራዊ ባደረጉ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በኩል አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዲጂታል አሰራር በተቋማቱ ለፅህፈት መሳሪያ ግዢ የሚወጣውን ወጪ በማስቀረት ሀብቱን ለሌላ ልማት እንዲውል ከማድረግ አንፃር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ ተገልጋዮች በቦታና በጊዜ ሳይገደቡ ባሉበት አካባቢ ሆነው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል።
ዜጎች አገልግሎት ለማግኘት የሚያባክኑትን ጊዜ፣ ገንዘብና የሙስና ተጋላጭነት እንደሚያስቀርም ተናግረዋል።
ቢሮው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም አቶ ሰላሙ ጠቁመዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው በክልሉ በስድስት የጤና ተቋማት ከወረቀት የጸዳ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በተቋማቱ የተጀመረው ዲጂታል አገልግሎት የታካሚዎችን እንግልት ለመቀነስ እንዲሁም የመረጃ አያያዝን ከማዘመን አንፃር የጎላ አስተዋጾ እያበረከተ መሆኑንም አመልክተዋል።
በመሆኑም ቢሮው ይህን አሰራር ለማጠናከር ከወረቀት ነፃ የሕክምና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሀድያ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን መምሪያ የተዘጋጀ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ኤግዚቢሽንና አውደርዕይ በሆሳዕና ከተማ ሰሞኑን በይፋ መከፈቱ የሚታወስ ነው።