የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በጋራ ለመሥራት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትና የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።
ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ቤተልሔም አበባውና የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ፈርመውታል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ጊዜ ኢንስቲትዩቱ የአየር ትንቢያ መረጃዎችን በማሰባሰብና በመተንተን በወቅቱ ተደራሽ እንዲሆኑ እየሰራ ነው።
ጎን ለጎንም የአየር ጠባይ አገልግሎት ተጠቃሚዎችም ሳይንሳዊ የሆነና ጥራት ያለው የአየር ጠባይ መረጃ ተደራሽ ለማድረግም ኢንስቲትዩቱ የአሰራር ማሻሻያች ማድረጉንም ነው ያስረዱት።
ጥራት ያለው የአየር ፀባይ መረጃዎን ተደራሽ ለማድረግ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ኢንስቲትዩቱ ዛሬ ከኢዜአ ጋር ሥምምነት ማድረጉን አስረድተዋል።
ሥምምነቱ ኢንስቲትዩቱ ጥራት ያለው የአየር ሁኔታና ጠባይ መረጃን በወቅቱ ለተቋማትና ለዜጎች ተደራሽ ለማደረግ እንደሚያስችለው ገልጸዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን ሥምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በትብብርና በቅንጅት በመሥራት የተሰጣቸውን አገራዊ ተልዕኮ ለመወጣት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ቤተልሔም አበባው በበኩላቸው ኢዜአ ተደራሽነቱን በማሳፋት መረጃዎችን በስፋት ለዜጎች እያደረሰ ነው ብለዋል።
ሥምምነቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያለውን ተደራሽነት፡ ልምድና የሰው ሃይል በመጠቀም ጥራት ያለው የአየር ጠባይ መረጃን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ሥምምነቱ ሀገርን ውጤታማ የሚያደርጉ ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።