የዘንድሮ የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን ግንቦት 27 እና 28 በተለያዩ መርኃ ግብሮች ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮ የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን ግንቦት 27 እና 28 በተለያዩ መርኃ ግብሮች ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦ የዘንድሮ የዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን "መሬትን ማገገም፣ በረሃማነትና ድርቅን መቋቋም" በሚል መሪ ኃሳብ ግንቦት 27 እና 28 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ መርኃ ግብሮች ይከበራል።
ቀኑ በኢትዮጵያ ለ31ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ51ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው።
ቀኑን የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ደን ልማትና የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በጋራ አዘጋጅተውታል።
በእለቱ አካባቢ ጥበቃና ብክለት መከላከልን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብር እንደሚካሄድ ተቋማቱ በጋራ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
በተጨማሪም አካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ጽዱና አረንጓዴ አካባቢ ለመፍጠር የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ ነው።
መንግሥት ለሕዝቡ ጤና ምቹና ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የግንዛቤ ሥራዎች ጨምሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሕዝቡ አካባቢውን ለማጽዳት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ተቋማትም ለአካባቢ ምቹ የሆነ የምርት ሂደት እንዲከተሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለአካባቢ መልሶ ማገገም ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር ከበደ ይማም ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በተሰራው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው፤ ይህም ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
ይህም ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው ሀገራት አካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ በበኩላቸው ብክለትን መከላከል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።