ቀጥታ፡

የኦሮሚያ ክልል ለ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለጸ

አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፡-የኦሮሚያ ክልል ለ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናዎች አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ገለጹ።

በክልሉ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ገዳማ የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ክልላዊ እና አገር አቀፍ ፈተና እንደሚወስዱም ተገልጿል።

ክልሉ ለ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናዎች ያደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ መግለጫ ሰጥተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ከ700 ሺህ በላይ የ6ኛ ክፍል ተማሪዎች እንዲሁም ከ600 ሺህ በላይ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ለፈተና ይቀመጣሉ።

የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ዘንድሮ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰጥ እንደመሆኑ መጠን የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የፊታችን ግንቦት 29 እና 30/ 2016 ዓ.ም የስድስተኛ ክፍል እንዲሁም ሰኔ 4 እና 5/ 2016 ዓ.ም ደግሞ የስምንተኛ ክፍል ፈተና የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም የፈተና ወረቀት  ወደ ዞንና ወረዳ ፈተና ጣቢያዎች ተጓጉዞ እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ አመቱን ሙሉ በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ከማድረግ ባለፈ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጣቸው መቆየቱንም ጠቁመዋል።

ከዚህም ባለፈ ተማሪዎቹ ራሳቸውን የሚፈትሹበት ሞዴል ፈተና መውሰዳቸውን ገልጸው ዘንድሮ ከተደረገው ቅድመ ዝግጅት አንጻር የተሻለ ውጤት የሚጠበቅ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ከ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አንጻርም ክልሉ ከ200 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ለፈተናው ዝግጁ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በተለይም ዘንድሮ ፈተናውን 'ኦን ላይን' ለመስጠት በተደረገው ጥረት በአንዳንድ ከተሞች በሚገኙ 40 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የማለማመድ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ተማሪዎቹን ዝግጁ የማድረጉና የማለማመዱ ስራ አሁንም የሚቀጥል መሆኑን ጠቅሰው በቂ ኮምፒዩተሮች በሌለባቸው አካባቢዎች ተማሪዎች በተለመደው መንገድ እንደሚፈተኑ ጠቁመዋል።

የፈተናዎቹ አሰጣጥ ሂደት የተሳካ እንዲሆን የትምህርት ማህበረሰቡ ጥረቱን እንዲያጠናክር እንዲሁም የጸጥታ አካላት የፈተና አካባቢን ሰላም በማረጋገጥ በኩል የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም የቢሮ ኃላፊው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም