የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የገለጻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የገለጻና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የምክክር ምዕራፍ እንዲሁም ቀጣይ ውይይቶችን አስመልክቶ ለባለድርሻ አካላት ገለጻና የገንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ ምሁራን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ማኅበራት ተወካዮች፣ ከሦስቱ የመንግሥት አካላት የተወከሉ ተወካዮች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተጀመረው የምክክር ምዕራፍ ከጠዋቱ መክፈቻ መርኃ ግብር በኋላ በነበረው ሂደት ተሳታፊዎች በየኅብረተሰብ ክፍላቸው በቡድን በመሆን ከወከሉት ማኅበረሰብ ያመጧቸው የአጀንዳ ኃሳቦች ላይ ውይይት እያደረጉ ሲሆን ዛሬ ይጠናቀቃል።
በሂደቱ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የኛ የሚሉትንና የተስማሙባቸውን የአጀንዳ ኃሳቦች በማጠናከር ለኮሚሽኑ በቃለ-ጉባኤ ተፈራርመው እንደሚያቀርቡም ይጠበቃል።
ያቀረቧቸው የአጀንዳ ኃሳቦች በቀጣዮቹ ቀናት በሚኖሩ መድረኮች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ይንፀባረቃሉ ተብሏል።
ተሰብሳቢዎች በቀጣዮቹ የምክክር ምዕራፎች ላይ የሚወክሏቸውን 121 ተወካዮች በመምረጥ ለሚቀጥሉት የምክክር ምዕራፎች እንደሚዘጋጁም ተጠቁሟል።
በመሆኑም እየተካሄደ ባለው የባለድርሻ አካላት መድረክ እስካሁን ያለው የምክክር ሂደት ላይ ገለጻ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ምክክሩ እስካሁን የመጣበትን ዋና ዋና ጉዳዮች አንስተዋል።
አጀንዳ ማሰባሰብ ከታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጀምሮ አካታች በሆነ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት በጋራ በሚኖራቸው ምክክር ለአጀንዳ ስብሰባው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ትኩረት የሚሰጠው እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የምክክር ምዕራፉ በቀጣዮቹ ቀናት ተጨማሪ የአራት ባለድርሻ አካላት ተወካዮችን በማሳተፍ እየተከናወነ እንደሚቀጥል የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር መሰረታዊ በሆኑ አገራዊና ፓለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የፖለቲካ መሪዎች ልዩነታቸውን በመግባባት እንዲፈቱ እድል በመፍጠር ትልቅ ፋይዳ አለው።
ቁልፍ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር፣ ዘላቂ ሰላም ማስፈን፣ ጠንካራና ቅቡልነት ላለው አገረ መንግሥት ግንባታ መደላድል መፍጠርም ሌላው የምክክሩ ዓላማ ነው።