የፍትህ ዘርፍ ሪፎርም የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የፍትህ ዘርፍ ሪፎርም የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ ነው - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 23/2016(ኢዜአ)፦የፍትህ ዘርፍ ሪፎርም መንግስት ትኩረት የሰጠው ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የአገራዊ የፍርድ ቤቶችና የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የ2016 በጀት ዓመት የ9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምግማ እየተካሄደ ነው።
የመድረኩ አላማ የአፈጻጸም ሂደቱን በመመልከት የመጡ ለውጦችን እና ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ የፍትህ ዘርፍና የዳኝነት አካሉን ሪፎርም ማድረግ የመንግስት ዋነኛ የትኩረት ትልቁ አጀንዳ እንደሆነ ገልጸዋል።
የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የፍትህ አካላት ሚና ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር ብቃት፣ ሥነምግባርና ክህሎት ባለው የሠው ኃይል ማደራጀት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን እንደሚገባም ገልፀዋል።
በመድረኩ ከአፈ ጉባኤ ታገሰ ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፣ የፌደራል እና የክልል ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣ የፌደራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች እና የፍትህ ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።