5ኛውን ዙር የኢትዮጵያ ስነ-ህዝብ እና ጤና ጥናት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው - በከር ሻሌ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
5ኛውን ዙር የኢትዮጵያ ስነ-ህዝብ እና ጤና ጥናት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ናቸው - በከር ሻሌ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ 5ኛውን ዙር የኢትዮጵያ ስነ -ህዝብ እና ጤና ጥናት ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) ገለፁ።
አገልግሎቱ በዛሬው እለት በቢሾፍቱ ከተማ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለተውጣጡ የመስክ መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) በስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ወቅት እንዳሉት፣ የስነ ህዝብ እና ጤና ጥናት ከህዝብና ቤቶች ቆጠራ ቀጥሎ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ዘርፍ ነው።
የጥናቱ ዋና አላማ ህዝብን መሰረት አድርገው ለሚቀረጹ ፖሊሲዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለማቅረብና ስራ ላይ ያሉ ፖሊሲዎች አፈጻጸምን ለመለካት የሚያግዙ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ነው ብለዋል፡፡
በጥናቱ የህጻናትና እናቶች ጤና እንክብካቤ፣ የአመጋገብ ስርዓት፣ የስነ ተዋልዶ መረጃ፣ የቤተሰብ ምጣኔ እና የኤች.አይ.ቪ ስርጭት መረጃዎች ተደራሽ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
ጥናቱ በመላው ሀገሪቱ ወካይ በሆነ ሳይንሳዊ የናሙና አመራረጥ ዘዴ በተመረጡ የጥናት ስፍራዎች እንደሚካሔድ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱን ለማካሄድ ከሃምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የመመሪያና የአፈጻጸም ቅደም ተከተሎች፣ መጠይቆች በአጠቃላይ ለጥናቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማሟላት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የቅድመ ዝግጅቱ የመጨረሻ ምዕራፍ የሆነው የመስክ መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያዎች ስልጠና ከዛሬ ግንቦት 22 እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ስልጠናው እንደተጠናቀቀ የመስክ ሰራተኞች ስምሪት እንደሚደረግ እና ለ5 ተከታታይ ወራት መረጃ የማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል፡፡
መረጃ አሰባሰቡ ቀላል እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ፈቃዱ ያደታ በበኩላቸው፤ የስነ ህዝብ እና የጤና ጥናት ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው ዘላቂ የልማት ግብ የደረሰችበትን ደረጃ ለመለካት ሚናው የጎላ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
በመሆኑም ጤና ሚኒስቴር ይህን መረጃ በወሳኝነት የሚጠብቀው በመሆኑ የመስክ ሰራተኞች በፍጹም ዲሲፕሊንና ስርዓቱን ተከትለው ስራቸውን እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
ጥናቱ በጤና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት እና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ትብብር የሚከናወን ሆኖ አይ-ሲ-ኤፍ የተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ደግሞ ለጥናቱ የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡