መገናኛ ብዙኃን ሀገር የመገንባትና ትውልድን በስነ-ምግባር የማነጽ ኃላፊነታቸውን በተጠናከረ መንገድ ሊወጡ ይገባል- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን ሀገር የመገንባትና ትውልድን በስነ-ምግባር የማነጽ ኃላፊነታቸውን በተጠናከረ መንገድ ሊወጡ ይገባል- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ መገናኛ ብዙኃን ሀገር የመገንባትና ትውልድን በስነ-ምግባር የማነጽ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ፡፡
የኤፍ ኤም አዲስ 97 ነጥብ 1 24ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሸጎሌ በሚገኘው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /ኢቢሲ/ ሚዲያ ኮምፕሌክስ የመጽሃፍ አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፍቷል።
አውደ ርዕዩ እስከ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚሁ ወቅት መገናኛ ብዙሃን በሀገር ግንባታ ሒደት ውስጥ የላቀ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ሁሉም መገናኛ ብዙሃን ሀገርን የመገንባትና ትውልድን በስነ-ምግባር የማነጽ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
ለሀገርና ህዝብ ጥቅም ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት የመገናኛ ብዙሃን መርህ ሊሆን እንደሚገባ ነው የጠቆሙት፡፡
ኤፍ. ኤም. አዲስ 97 ነጥብ 1 ለህብረተሰቡ መረጃን በማቅረብ ረገድ በርካታ ስራዎችን እንዳከናወነም ነው ያነሱት፡፡
በቀጣይም የሬዲዮ ጣቢያው ሀገርና ህዝብን የማገልገል ኃላፊነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ሬዲዮ ጣቢያው የሚያስተላልፋቸውን ፕሮግራሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በዛሬው እለት የተከፈተው አውደ ርዕይም አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን /ኢቢሲ /ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌትነት ታደሰ፤ ተቋሙ አዳዲስ የይዘትና የአቀራረብ ስልቶችን ይዞ የተሻሉ መረጃዎችን ለሕዝብ ለማድረስ እየሰራ ነው ብለዋል።
ከዚህ ውስጥም “ኢቢሲ ወደ ይዘት“ በሚል ሀገራዊ መግባባትን በኢትዮጵያ አንድነት እና መቀራረብ የሚፈጥሩ አዳዲስ የይዘት እና አቀራረቦችን ይዞ በቅርቡ ወደስራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ለአድማጭ እና ተመልካች ማህበረሰብ የሚጠቅሙ ይዘቶችን ለማድረስ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡