የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የእሳት አደጋ ብርጌድ በማደራጀት ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ ነው 

ሀዋሳ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የእሳት አደጋ ብርጌድ በማደራጀት ለሀዋሳና አቅራቢያው ለሚገኙ ከተሞች በሚሰጠው አገልግሎት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስታወቀ።

ፓርኩ ዓለም አቀፉን የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።

በፓርኩ የኦፕሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ በልአንተ ጠብቀው ለኢዜአ እንደገለጹት ፓርኩ ባደራጀው የእሳት አደጋ ብርጌድ ከራሱ አልፎ ለሀዋሳ ከተማና አቅራቢያ ለሚገኙ ከተሞች አገልግሎት እየሰጠ ነው ።

ፓርኩ ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎችን በመመደብና ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ወደስራ በማስገባት የሚጠበቅበትን ማህበራዊ ሃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

"አሁን ላይ ፓርኩ ከ60 በሚበልጡ የሰለጠኑ ባለሙያዎች፣ በሶስት የእሳት አደጋ መከላከያ ተሸከርካሪዎችና በሁለት አምቡላንሶች በመታገዝ  የእሳት አደጋን የመከላከልና መቆጣጠር ተግባር እያከናወነ ነው" ብለዋል።

በፓርኩ የቅድመ አደጋ መከላከል አስተባባሪ አቶ ደረጃው አምሳሉ በበኩላቸው በፓርኩ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

"በፓርኩ ታስቦ የዋለው የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ቀን 24 ሰዓት ለሚሰሩና ህይወትና ንብረት ለማዳን የሚተጉ ባለሙያዎችን የሚያበረታታ ነው" ብለዋል።

ላለፉት ሰባት ዓመታት ከፓርኩ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ በማገልገል ሙያዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የገለጸው ደግሞ በፓርኩ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ባለሙያ ወጣት ዝናቡ ወሽኔ ነው።


 

ሙያው ከሰው ህይወትና ንብረት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑን ገልጾ "ቀኑ በፓርኩ መታሰቡ ሙያው የሚጠይቀውን ስነምግባር ተከትሎ የበለጠ ለማገልገል ያዘጋጃል" ብሏል።

ሌላኛው የእሳት አደጋ ባለሙያ ዳርሰማ ሸምሱ በበኩሉ ፓርኩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ ሙያዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት እንደ አደጋ ጊዜ ሰራተኛ በሙሉ አቅሙ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።


 

ቀኑን ከባለሙያ ጋር አስቦ መዋል የበለጠ መስራት የሚያስችል ተነሳሽነት የሚፈጥር በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ጠቅሶ የእሳት አደጋን ለመከላከልና መቆጣጠር ለሚከናውነው ተግባር ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል ።

ዓለም አቀፉ የእሳት አደጋ ባለሙያዎች ቀን "የእሳት አደጋ ባለሙያ የህዝብ አገልጋይ ነው" በሚል  መሪ ቃል በፓርኩ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል ፡፡

በዝግጅቱም የፓርኩ ሰራተኞችና አመራሮች የተገኙ ሲሆን ለፓርኩ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ለሚያደርጉት የህይወት አድን ተጋድሎ የዕውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ120 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች የስራ ዕድል የፈጠረ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም