በክልሉ ለጋራ ዕድገትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ አስተዋጾ ላላቸው እሴቶች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው

ሚዛን አማን ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለጋራ ዕድገትና ዘላቂ ሰላም ግንባታ አስተዋጾ ላላቸው እሴቶች ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አስታወቀ። 

ምክር ቤቱ ሁለተኛ ዓመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን በቴፒ ከተማ አካሂዷል።

የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ መቱ አኩ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት የሕዝቦችን የአብሮነት እሴት ማጎልበት ከተቻለ ዘላቂ ሰላምና ፍትሃዊ ልማትን ማረጋገጥ ይቻላል።

በእዚህም ምክር ቤቱ በክልሉ የጋራ ዕድገትና ዘላቂ ሰላም የሚያግዙና የሚያስተሳስሩ እሴቶች ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ክልል የጋራ አድገትን ለማምጣት የሚያስችሉ ባህላዊ እሴቶችና ጸጋዎች እንዳሉ ያስታወሱት አቶ መቱ፣ እነዚህን ለማጠናከር ለማስተማር ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ሕዝብ አንድነቱን የሚያጠናክሩ መልካም እሴቶቹን እንዲያውቅ ለማድረግ የምክር ቤት አባላት ስልጠና ወስደው የህዝብን ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ያሉ 13 ብሔረሰቦች የራሳቸው ታሪክ፣ ወግና ባህል ቢኖራቸወም ተመሳሳይ ሥነ ልቦና እና የአኗኗር ዘዬ እንዳላቸው የገለጹት ደግሞ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አባል አቶ ባህሩ ወልደጊዮርጊስ ናቸው።

ለዘላቂ ሰላምና ልማት የሚያግዙ መልካም ባህሎችና ወጎች እያሉን መቸገር የለብንም ያሉት ደግሞ ሌላዋ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ፀሐይ አየለ ናቸው።

በብሔረሰቦች መካከል እርስ በርስ መከባበር፣ ፍቅር እና አብሮነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የቆዩ ባህልና እሴቶችን ወደ ህብረተሰቡ ለማስረጽ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ተስፋዬ መኩሪያ በበኩላቸው "እንደ ብሔረሰብ ምክር ቤት አባል የክልሉን ህዝብ አንድነት ለማጠናከር ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ የመስራት ኃላፊነት አለብን" ብለዋል።

የሕዝቡ የልማትና የሰላም ግንባታ ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ ቋንቋውን እና ባህሉን እንዲያለማ ከምክርቤቱ አባላት ብዙ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም