የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ አቅሙን ከ70 ቢሊየን ዶላር በላይ ለማሳደግ የሚያስችለውን የአስር ዓመት ስትራቴጂ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ልማት ባንክ የፋይናንስ አቅሙን ከ70 ቢሊየን ዶላር  በላይ ለማሳደግ የሚያስችለውን የአስር ዓመት ስትራቴጂ ይፋ አደረገ፡፡ 

ባንኩ በኬንያ ናይሮቢ እያካሄደ ባለው ዓመታዊ ጉባኤ እስከ 2033 የሚተገብረውን አዲስ የአስር ዓመት ስትራቴጂ ይፋ አድርጓል።

ስትራቴጂው የበለጸገች፣ አካታች፣ ተጽእኖን መቋቋም የምትችልና አንድነቷ የተጠናከረ አፍሪካን ለመፍጠር የተቀመጠውን ራዕይ ታሳቢ ያደረገ ነው።

በአፍሪካ ላይ የሚደረጉ ጫናዎችን በመቋቋም ወደ ዘላቂ ምጣኔ ሃብት እድገትና ብልጽግና ለማምጣት የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ እንደሆነም ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ ለአፍሪካ ማህበራዊ ምጣኔ ሃብት ሽግግር አፍሪካ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ከግምት ያስገባ ነው።


 

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና ባንኩ የአፍሪካ የልማት ፋይናንስ ተቋም እንደመሆኑ  በቀጣይ አስር ዓመታት የሚያደርገው ድጋፍ አህጉሩን ለማሸጋገር ወሳኝ ነው ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ-19 ያስከተለው ዘርፈ ብዙ ተጽእኖ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋት አህጉሩን እየፈተኑ ከሚገኙ ተግዳሮቶች ውስጥ ዘርዝረዋል።

ከዚህ አኳያ የአስር አመት ስትራቴጂው የአፍሪካ አገራት ቀጣናዊና አለም አቀፍ ችግሮችን መቋቋም እንዲችሉ ድጋፍ ለማድረግ ባንኩ የሚወስዳቸውን ወሳኝና አስቸኳይ እርምጃዎችን ያስቀመጠ ነው ብለዋል፡፡

የሚወሰዱ እርምጃዎች የአፍሪካን የተለያዩ ሃብቶች በማሳደግ አጀንዳ 2063 እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት የሚያስችሉ ናቸው። 

አፍሪካ ያላት ወጣትና አምራች የሰው ሃይል፤ አንዲሁም በፍጥነት እያደገ ያለውን የገበያ አቅም በማሳደግና  ከብክለት የጸዳ የሃይል ምንጭ በማቅረብ  አህጉሪቷ ከራሷ ባለፈ ለዓለም ችግሮች መፍትሄ እንድትሆን ማስቻል ደግሞ የስትራቴጂው ማዕከል መሆኑን አንስተዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዝዳንት የአፍሪካ ህዝብ በፍጥነት እያደገ መሆኑን በመጠቆም የአስር አመት ስትራቴጂው በሴቶችና ወጣቶች ላይ  መዋለነዋዩን የሚያፈስባቸው ጉዳዮችን መለየቱን ጨምረዋል።

ባለፉት አስር አመታት በሃይል፣ በምግብ ራስን በመቻል፣ በኢንዱስትሪ፣ በአህጉራዊ ትስስር፣ የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል የተገኙ ስኬቶችን በማስፋት እንደሚሰራ ተገልጿል።

ሴቶች እና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢንቨስትመንትን መተግበር፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ መስጠት፣ መልካም አስተዳደርን ማበረታታትና የተረጋጋ ምጣኔ ሃብት እውን ማድረግ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ተዘርዝረዋል። 

ለአፍሪካ ምጣኔ ሃብት ሽግግር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በማምረቻው፣ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች  በቀጣይ አስር አመታት አጋርነትን በማጠናከር የሚሰራባቸው ዘርፎች ናቸው።

ከዚህ ጋር በተያያዘም በ2033 ለግሉ ዘርፍ የሚደረግ ፋይናንስን በሶስት እጥፍ ለማሳደግ ውጥን መያዙን ተናግረዋል፡፡

ባንኩ ከግሉ ዘርፍ ጋር ከሚያደርገው አጋርነት ባለፈ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የፋይናንስ አቅሙን ለማሳደግ እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም