በሠመራ  ከተማ  የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የውሃ አጠቃቀምን  የሚያስተዋውቅ  ዐውደ ርዕይ  ተከፈተ

ሠመራ ፤ ግንቦት 22/2016 (ኢዜአ)፦  የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የውሃ አጠቃቀምን የሚያስተዋውቅ  ባዛርና ዐውደ ርዕይ ዛሬ  በሠመራ ተከፍቷል።

በባዛሩና ዐውደ ርዕዩ በክልሉ ከሚገኙ ሰባት ወረዳዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አቅራቢዎች ተሳትፈዋል።

ፈሳሽና የዱቄት ሳሙናዎች፣  የውሃ ማከሚያዎች፣ በፀሐይ የሚሰሩ ጄኔሬተሮች፣ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እንዲሁም ለመፀዳጃ አገልግሎት መሥጠት የሚችሉ የእጅ መታጠቢያ ሳህኖች ደግሞ በባዛሩ ላይ የቀረቡት የምርት ዓይነቶች ናቸው።


 

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ዊቲካ ኖሬ በዚህ ወቅት እንደገለፁት የህብረተሰባችን የአኗኗር ስልትና የአየር ንብረቱን ባማከለ ሁኔታ የቀረቡት የንፅህና መጠበቂያ ቁሶች  ለቅድመ መከላከል የጤና ስርአት  የጎላ  ፋይዳ አላቸው ።

"ወጣቶች የራሳቸውን ምርት ይዘው መቅረባቸው  የሚበረታታ ነው" ያሉት አቶ ዊቲካ፤ ይህ ባዛርና ዐውደ ርዕይ ህብረተሰቡ እነዚህን ጠቃሚ ቁሳቁሶች በስፋት እንዲያገኝ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል  የሚያስችሉትን እነዚህን የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦት በቀጣይነት ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን ከዚህም በላቀ እንዲስፋፋ ይደረጋል ብለዋል።

በዚሁ ዕለት የተገኙት የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መሐመድ ያዬ በበኩላቸው መሰል የባዛርና ዐውደ ርዕይ ዝግጅቶች በሌሎች አካባቢዎችም መቀጠል አለባቸው።

ባዛሩ በዚህ የንፅህና መጠበቂያ ዘርፍ ተደራጅተው የተሠማሩት ወጣቶች ወደ ገበያ ወጥተው ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁና በስፋት እንዲያቀርቡ ከማድረግ ባለፈ ለገበያ ዋጋ መረጋጋቱም ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

የንጽህና መጠበቂያ ምርት ይዘው በባዛሩ ላይ ከቀረቡት መካከል ከጓደኞቿ ጋር ፈሣሽ ሣሙና በማምረት በዱብቲ፣ ሰመራ ሎጊያ፣ ዴትና ሌሎችም የገጠር ቀበሌዎች ምርቶች በማቅረብ ላይ መሆናቸውን የገለጸችው ወይዘሮ ጀሚላ አህመድ ባዛሩ ይበልጥ ተደራሽ ለመሆን ያግዘናል ብላለች።

ከአሁን ቀደም ድጋፍ እና እገዛ ተደርጎላት ስልጠና በማግኘት የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ መሥራት የቻለችው ሐዋ መሐመድ ደግሞ የመጣችው ከጭፍራ ወረዳ ነው።

ቁሳቁሱን የአርብቶ አደር ሴቶችም ጭምር መጠቀም የሚችሉበት አጋጣሚ በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሏን ገልጻ፤ አሁን የተዘጋጀው ባዛር ደግሞ የበለጠ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ እንደረዳቸው ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም