በክልሉ ፍትሓዊነትን ያማከሉ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - አቶ አሻድሊ ሐሰን 

አሶሳ፤ ግንቦት 22/2016 (ኢዜአ):- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የህዝቡን ፍትሓዊ ተጠቃሚነት ባማከለ መልኩ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ተናገሩ::

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ አሶሳ ዞን ከኡራ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር ዛሬ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል::

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት የክልሉ ሠላም አስተማማኝ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም የህብረተሰቡ አንድነት እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።

ይህም ክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት በጋራ ለማልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በማዕድናት፣ በግብርና እና ሌሎችም ልማቶች  ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያማከለ ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

በተለይም በግብርናው ዘርፍ በመስኖ በመታገዝ ያመረቱት አርሶ አደሮች፤ ከራሳቸው አልፈው ገበያን በማረጋጋት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ  በአብነት  ጠቅሰዋል::

ይህን ተጠቃሚነት ለማጠናከር የክልሉ መንግስት ሰላሙን ከማጽናት በተጓዳኝ የመንገድ፣ የጤና፣ የውሃ፣ የመስኖ ግድቦችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋት ጥረት እያደረገ መሆኑን  ገልጸዋል::


 

የኡራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንድሪስ አልመሃዲ በበኩላቸው በቅርቡ በአዲስ መልክ የተዋቀረው ወረዳው የህዝቡን ፍላጎት ትኩረት በማድረግ በተለይም መሠረተ ልማቶችን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል::

ህብረተሰቡም የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በልማቱ በንቃት መሳተፍ እንዳለበትም አቶ እንድሪስ ጥሪ አቅርበዋል።

ከኡራ ወረዳ በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት አቶ አማረ አሰፋም የክልሉ መንግስት ህብረተሰቡን ከማቀራረብ ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል::

በውይይቱ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላትና የወረዳው ነዋሪዎች ተገኝተዋል:: 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም