ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በፋይናንስና በሰው ኃይል ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው- የጎንደርና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በፋይናንስና በሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰሩ መሆኑን የጎንደርና ቦንጋ ዩኒቨርሲቲዎች ገለፁ።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ራስ ገዝ መሆን የሚችሉበትን መንገድ በጥናት በመለየት የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች አዋጅ 1294/2015 መፅደቁ ይታወሳል።

ራስ ገዝ መሆን ዩኒቨርሲቲዎች በአስተዳደራዊ፣ በአካዳሚክ፣ በሰው ኃብትና ፋይናንስ አስተዳደር ጉዳዮች ነፃነትን ከተጠያቂነት ጋር የሚያገኙበት የአሰራር ስርዓት ነው።

የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን የተቋማቱን ብቃት በማሳደግ የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች በክህሎት፣ አመለካከትና እውቀት የተሟላ ነገር ይዘው እንዲወጡ ያስችላል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ለኢዜአ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ በተደረገው ልየታ የምርምር ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተከትሎ ምርምር ላይ በማተኮር እየሰራ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው ራስገዝ ለመሆን ገቢ የሚያመነጭበትን መንገድና የአሰራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት ላይ እየሰራ እንደሆነም ነው የገለፁት።

ዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ አቅሙን ለማጎልበት ከተልዕኮው ጋር ሊሄዱ የሚችሉ የገቢ ማስገኛ ተቋማትን እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከ2013 ጀምሮ የራሱን ገቢ ማመንጫ በቦርድ አፀድቆ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመው በዚህም እቴጌ ምንትዋብ የንግድና ማማከር አገልግሎት የተሰኘ ተቋም መቋቋሙን ገልፀዋል።

ተቋሙ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን በስሩ የሚገኙ ተማሪዎች ተግባር ተኮር ትምህርት ማግኘት የሚችሉበትና ገቢ ማግኘት የሚያስችሉ ዘጠኝ ተቋማትን መመስረቱንም አስረድተዋል።          

ራስገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የሚያስፈልጉ የተለያዩ መመሪያዎች ረቂቅ መዘጋጀቱን ገልፀው በርካታ መምህራን የማስተርስና ፒኤችዲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነም ተናግረዋል።

ራስገዝ ለመሆን ከአጋር አካላት ድጋፍ እያገኙ እንደሆነና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተሞክሮውን በማካፈል እያገዛቸው እንደሚገኝ አንስተዋል።

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ(ዶ/ር) በበኩላቸው ራስ ገዝ ለመሆን በሰው ሀብት ልማት ላይ እየተሰራ መሆኑንና በዚህም ከ70 በላይ መምህራን በፒኤችዲና በማስተርስ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነ ነው ያስረዱት።


 

በገንዘብ ያለውን አቅም ለማሳደግ እንዲቻል 17 የምርምር ፕሮጀክቶች ከወረቀት አልፈው ወደተግባር ተቀይረው ገቢ ማስገኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በቡና ልማት፣ በወተትና የጊደር ዝርያ፣ ዶሮ፣ ቅመማ ቅመም እንዲሁም ፍራፍሬ ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ ባሻገር በዩኒቨርሲቲው የውስጥ ገቢ የተሰራ 18 ክፍል ያለው ባለአንድ ወለል ህንፃ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች በማከራየት ገቢ እየተገኘበት መሆኑንም ገልፀዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሚተዳደሩ 20 ሎጆች የዩኒቨርሲቲውን ገቢ በማሳደግ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆናቸውን አንስተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም