ከተሞችን ፅዱና ውብ ለማድረግ ለተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄ ስኬታማነት ዜጎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

ሀዋሳ  ፤ ግንቦት 22/2016 (ኢዜአ)፦ - ከተሞችን ፅዱና ውብ ለማድረግ ለተጀመረው ሀገራዊ ንቅናቄ ስኬታማነት ዜጎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘው ተሻገር አሳሰቡ።

በሀዋሳ ከተማ "ፅዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደ ክልል አቀፍ ፅዱ ከተሞችን የመፍጠር ንቅናቄ ማስጀመሪያና የገቢ ማሰባሰብ መርሀ ግብር ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተገኝቷል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የንቅናቄ ሥራው በሀገር አቀፍ ደረጃ ፅዱና አረንጓዴ ከተሞችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ መፀዳጃ ቤቶች በስፋትና በጥራት ለማዘጋጀት ጭምር ታስቦ እየተካሄደ መሆኑን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ከተሞች የነዋሪዎቻቸውን እና የእንግዶቻቸውን ክብር በሚመጥን መልኩ ፅዱና ውብ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ጽዱ ጎዳና ኑሮ በጤና" መርሀግብር በሀገር ደረጃ በይፋ ከተጀመረ በኋላ ሰፊ የንቅናቄ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውሰው፣ የዜጎች ተሳትፎም የላቀ ነው ብለዋል።

ለአብነት ለመርሀግብሩ በአንድ ጀንበር 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በተከናወነው የንቅናቄ ሥራ 150 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ መቻሉን አስታውሰዋል።

በአሁን ወቅት በሁሉም አካባቢዎች በክልል ደረጃ ፅዱ ከተሞችን የመፍጠር ንቅናቄ መጀመሩን ጠቁመው፣ በዚህም ከተሞችን ፅዱና ውብ ለማድረግ ለተጀመረው ንቅናቄ ስኬታማነት ዜጎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።

የሲዳማ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርን ጨምሮ በተለያዩ ልማቶች ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ አገኘሁ፣ ፅዱ ከተሞችን በመፍጠር በኩልም ስኬታማ ሥራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ከተሞች በቱሪስት ተመራጭነቷ ግንባር ቀደም እንደሆነች ጠቅሰው፣ ማራኪ ዕይታዎችን ማጠናከር እንዲሁም ምቹና ፅዱ መፀዳጃ ቤቶችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ባሉ ከተሞች ህብረተሰቡ አካባቢውን አረንጓዴና ፅዱ አድርጎ የመጠበቅ ልምድ እንዳለው አስታውሰዋል።


 

ይሁንና ፅዱ ከተሞችን የመፍጠሩ ሥራ የተሟላ እንዲሆን ያለንን ልምድ ማስፋትና ተባበብረን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

"በልማት ከተባብርን ንቅናቄውን በአግባቡ በመምራት ከተሞቻችንን ጽዱና ማራኪ አድርገን መገንባት እንችላለን" ብለዋል።

የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በከተማዋ 411 የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች እንዳሉ ገልጸው፣ 70 ዎቹን በተሻለ የጥራት ደረጃ ገንብቶ ለአገልግሎት ለማብቃት በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ሀዋሳ በሰፋፊ መንገዶቿና በአረንጓዴ ልማት ሥራ ተጠቃሽ መሆኗንም አስታውሰዋል።

በአሁን ወቅት የከተማዋ የአረንጓዴ ልማት ሽፋን 27 በመቶ መሆኑንና ይህንን ከ30 በመቶ በላይ ለማድረስ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

ሥራውን በህዝብ ተሳትፎ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲቻል የሀዋሳ ከተማ ልማት ምክር ቤት ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሩ ላይ ከተሳተፉ ባለሀብቶች መካከል የቤዛ የተፈጥሮ ምንጭ ውሃ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ይርጋለም አስፋው ድርጅታቸው ለዚህ ሥራ አንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

"ሀዋሳ ከዚህ ቀደምም በፅዳትና ውበቷ ተቀዳሚ ነች ያሉት ወይዘሮ ይርጋለም ከዚህም በበለጠ ፅዱ ፣ ማራኪና ለኑሮ ምቹ ሆና እንድትቀጥል የሁላችንም ድጋፍ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለሀብቶች የተገኙ ሲሆን ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም