በኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ምቹ ምህዳር መፍጠር የሚያስችሉ ህጎች ገቢራዊ እየተደረጉ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 22/2016(ኢዜአ)፦  በኢትዮጵያ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ ኢንቨስትመንት ምቹና የተሳለጠ ምህዳር መፍጠር የሚያስችሉ ህጎችና አሰራሮች ገቢራዊ እየተደረጉ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ "ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ 2024" የተሰኘ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አውደ ርዕይና ሲምፖዚየም በሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ መርቀው ከፍተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ ፤ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በመሠረተ ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ፈጠራን በማጎልበት የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆኑ በአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ያለው ድርሻ 21 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለፉት ዓመታት ከነበረበት 166 ሺህ ኪሎ ሜትር ወደ 246 ሺህ ኪሎ ሜትር ማደጉን ጠቁመዋል፡፡


 

ሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ልዩ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው፤ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎም እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡

በዚህም ለግሉ ዘርፍ የነበረው የብድር አቅርቦት በ2009 ዓ.ም ከነበረበት 41 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ አሁን ላይ ወደ  62 በመቶ አድጓል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ በኮንስትራክሽን ዘርፉ የተሰወዱ የማሻሻያ ርምጃዎች ተወዳዳሪዎችን በማበረታታት የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች ያለች ሀገር መሆኗን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘርፉ በቀጣይ አራት ዓመታት በየዓመቱ 8 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡


 

በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ መሠረት የመንገድ፣ የባቡር፣ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ግንባታ ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት የኮንስትራክሽን ኢንቨስትመንት ዘርፉን በማዘመን ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለመሳብ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዘርፉ እድገት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከመቀበልም ባለፈ መስጠት የሚያስችል ጸጋ ያላት ሀገር በመሆኗ ለዘርፉ  ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው  እድገትና ብልጽግና ላይ ለመድረስ በቀረፀቻቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ሀገራዊ የኮንስትራክሽን ልማት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከፍተኛ ሀብት የሚንቀሳቀስበት በርካታ ተዋንያን የሚሳተፉበት በመሆኑ ለኢንዱስትሪ ቱሪዝም መስፋፋት ያለው አበርክቶም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ዘርፉ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫዎት ገልጸው፤ ለዚህም ዓለም የደረሰበትን የግንባታ ቴክኖሎጂ ገቢራዊ ማድረግ እና በትብብር መስራት ግድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ 80 በመቶ የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ማቅረብ የሚያስችል አቅም መፈጠሩን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር ዘርፉን ለማዘመን ያግዛል ብለዋል፡፡


 

በዘንድሮው የቢግ 5 ኮንስትራክት አውደ ርዕይ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተዋንያን እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል፡፡

በአውደ ርዕይው ከሚቀርበው ትርኢት ባለፈ ዘርፉን በእውቀትና በምርምር መደገፍ የሚያስችሉ የፓናል ውይይቶች ይካሄዳሉም ነው ያሉት፡፡

የመጀመሪያው ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ በርካታ ኩባንያዎች በተገኙበት በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም መካሄዱ ይታወቃል።

ከዛሬ ግንቦት 22-24/2016 ዓ.ም የሚካሄደውን አውደ ርዕይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአጋር አካላት ጋር አዘጋጅተውታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም