በክልሉ ከ469 ሺህ በላይ ሰዎችን ከጎርፍ ለመታደግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው

ባህር ዳር ፣ግንቦት 22/2016 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በክረምት ወቅት ሊከሰት ከሚችል የጎርፍ አደጋ ከ469 ሺህ በላይ ሰዎችን ለመታደግ የሚያስችል የዝግጅት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለፀ።

የኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክረምት ወቅት የጎርፍ አደጋ የሚከሰትባቸውን ቦታዎች በመለየት የጎርፍ መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

ለጎርፍ መከላከል ስራዎቹም ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በክንውን ላይ  እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የጎርፍ መከላከል ስራዎቹ እየተሰሩ ያሉትም በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ፣ ሊሞ ከምከም እና ፎገራ ወረዳዎች፤  በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ዙሪያ፣ ምእራብ እና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች እንዲሁም በምዕራብ እና ምስራቅ አማራ በሚገኙ አካባቢዎች ላይ እንደሆነም ገልፀዋል።

በተጠቀሱት አካባቢዎችም ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑና በጥናት የተለዩ 22 የከተማ አስተዳደሮች እና ወረዳዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

የዝግጅት ስራው በአካባቢው የሚኖሩና ለማህበራዊ አገልግሎት ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ከ469 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ከጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ ለመከላከል እንደሚያስችል ገልፀዋል።

በተጨማሪም የጎርፍ መከላከል ስራው 15 ሺህ የመኖርያ ቤቶችን እና 218 ሺህ የቤት እንስሳትንም ከጎርፍ አደጋ ለመታደግ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

እየተሰሩ ካሉት ስራዎች መካከልም የክትር ስራ፣ በማሽን የታገዘ የጎርፍ መቀልበሻ ግድብና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

እስካሁን በተሰሩ ስራዎች የተገባደዱ ተግባራት እንዳሉ ገልፀው ቀሪዎቹን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ/ም ድረስ ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቁ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

ህብረተሰቡ የሚሰሩ የጎርፍ መከላከያ ስራዎችን ከማገዝ ባለፈ በጥንቃቄ በመያዝ ዘላቂነታቸውን ማረጋገጥ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም